አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 15፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የታለመለት የነዳጅ ድጎማ አገልግሎት ለማግኘት 134 ሺህ 684 ተሽከርካሪዎች መመዝገባቸውን ኢትዮ ቴሌኮም አስታወቀ፡፡
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬ ህይወት ታምሩ በሰጡት ማብራሪያ÷ የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር በድጎማው ተጠቃሚ ይሆናሉ ብሎ ከጠበቃቸው ከ164 ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎች መካከል በኢትዮ ቴሌኮም ሲስተም 134 ሺህ 684 የሚሆኑት ተመዝግበዋል፡፡
አገልግሎቱን ለማግኘት ከተመዘገቡት ተሽከርካሪዎች መካከል፥ 26 ሺህ 849 ያህሉ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
እስካሁን በቴሌብር ከነዳጅ ግብይት ጋር በተያያዘ 104 ሚሊየን ብር ዝውውር መደረጉን ጠቁመው÷ ከዚህ ውስጥ ከ95 ሚሊየን ብር በላይ የሚሆነው የድጎማው አካል መሆኑን አብራርተዋል፡፡
አገልግሎቱን ለማግኘት ተመዝግበው የድጎማው ተጠቃሚ መሆን ያልቻሉት መረጃቸው ተሟልቶ ባለመቅረቡ እና በመረጃ ማጣራት ምክንያት በተፈጠረ ክፍተት መሆኑንም ነው ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ያስታወቁት፡፡
አገልግሎቱን ለማሳለጥም 2 ሺህ 548 ሠራተኞች በተለያዩ ማደያዎች ተመድበው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እየሠሩ መሆናቸውን አመላክተዋል።
መንግስት ሕገ ወጥ የነዳጅ ግብይትን ለመከላከል የታለመለት የነዳጅ ድጎማን ተግባራዊ ማድረግ ከጀመረ 16ኛ ቀኑን መያዙ ተመላክቷል፡፡
በመሳፍንት እያዩ እና በቃለአብ ግርማ
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!