አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 15 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ዩክሬን የእህል ምርቷን በጥቁር ባህር በኩል ለውጭ ገበያ እንድታቀርብ የሚያስችል ስምምነት ከሩሲያ ጋር ተፈረመ።
ስምምነቱ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ፣ የቱርኩ ፕሬዚዳንት ሬሲፕ ታይፕ ኤርዶኻን እና የሩሲያ እና ዩክሬን ተወካዮች በተገኙበት በቱርክ ኢስታንቡል ነው የተፈረመው።
ስምምነቱ ከሩሲያ ዩክሬን ጦርነት በኋላ በኦዴሳ ወደብ ተከማችቶ የቆየውን የዩክሬንን 20 ሚሊየን ቶን ጥራጥሬ ምርት ለዓለም ገበያ እንዲቀርብ የሚያስችል ነው ተብሏል።
ከስምምነቱ መፈረም በኋላ ዓለም አቀፍ የጥራጥሬ ዋጋ ላይ ቅናሽ ማሳየቱ እየተነገረ ነው።
በስምምነቱ መሰረት ጥራጥሬ የጫኑ የዩክሬን መርከቦች ያለምንም ገደብ እንዲንቀሳቀሱ ሲፈቀድላቸው ሩሲያም መርከቦቹ እህል ጭነው በሚጓዙበት ወቅት የተኩስ አቁም ታደርጋለች።
ከዩክሬን ባለፈም ሩሲያም የጥራጥሬ እና ማዳበሪያ ምርቶቿን በጥቁር ባሕር በኩል ለዓለም ገበያ የምታቀርብበትን መንገድ ማመቻቸትም የስምምነቱ አካል መሆኑም ነው የተገለጸው።
ቱርክም በተመድ ድጋፍ እየተደረገላት በአካባቢው የመሳሪያ ዝውውር እንዳይኖር በሚል ከሩሲያ በኩል የተነሳውን ስጋት ለመቅረፍ በመርከቦቹ ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ታደርጋለች ነው የተባለው።
የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረበት ካለፈው የካቲት ወር ጀምሮ የጥራጥሬ ምርት ለዓለም ገበያ እየቀረበ አይደለም።
ለዚህ ደግሞ ዩክሬን ሩሲያ የጥቁር ባሕር ወደቦችን ዘግታብኛለች በሚል ስትኮንን በአንጻሩ ሩሲያ ውንጀላውን ስታስተባብል ቆይታለች።
ዛሬ የተደረሰው ስምምነትም “በጦርነቱ የተገኘ ትልቅ የዲፕሎማሲ ድል” ተብሎለታል።