አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 17፣ 2014 (ኤፍ ቢሲ) በካሊፎርኒያ ኦክ የደረሰው የእሳት አደጋ በርካታ መኖሪያ ቤቶችን አወደመ።
የእሳት አደጋው በትላንትናው ምሽት በግዛቷ መስፋፈቱን ተከትሎም ከ6 ሺህ በላይ ነዋሪዎች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ መጠየቃቸው ነው የተዘገበው፡፡
በአደጋው ቢያንስ አስር ህንጻዎች ሙሉ በሙሉ መውደማቸው የተገለፀ ሲሆን፥ ከ2 ሺህ በላይ ህንፃዎች አደጋ ላይ ናቸው ተብሏል፡፡
አርብ የተከሰተውን የእሳት አደጋ የመከላከል ጥረት ቢደረግም እስከ ቅዳሜ ከሰዓት ባለው ጊዜ 6 ሺህ ሄክታር ቦታ ማቃጠሉን ሲጅቲኤን ዘግቧል፡፡
አሁን ላይ የእሳት አደጋውን መስፋፋት ለማስቆም ከ400 በላይ የእሳት አደጋ ሰራተኞች እየተረባረቡ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፥ የእሳት አደጋው ምክንያት እየተጣራ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
ቀደም ሲል በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በበርካታ የአውሮፓ ሀገራት የተከሰተው ከፍተኛ ሙቀት በቀሰቀሰው ሰደድ እሳት ከፍተኛ ውድመት እያስከተለ መሆኑ ተዘግቧል፡፡
አሁን ላይ በአውሮፓ ደኖች ላይ የተቀሰቀሰው የሰደድ እሳት ተባብሶ ቀጥሏልም ነው የተባለው፡፡
የዓለም የሚቲዮሮሎጂ ድርጅት ኃላፊ ፔቴሪ ታላስ ስለጉዳዩ በሰጡት መግለጫም፥ ከዚህ በኋላ የሙቀት ማዕበል በአውሮፓ የሚስተዋል ይሆናል፤ ከአሁኑ የባሰ ተፅዕኖም ሊያስከትል ይችላል ብለዋል፡፡
የሙቀት ማዕበሉ በብሪታኒያ፣ ፈረንሳይ ፣ ጀርመን ፣ ቤልጂዬም፣ ኔዘርላንድስ፣ ግሪክ፣ ስፔን እና ጣልያንን ጨምሮ በበርካታ ሀገራት መከሰቱን ሲጅቲኤን እና ቢቢሲ ዘግበዋል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!