የሀገር ውስጥ ዜና

ብሔራዊ የታለመለት የነዳጅ ድጎማን በተመለከተ መልካም ጅምሮችን ማስፋት እንደሚያስፈልግ ተጠቆመ

By Meseret Awoke

July 24, 2022

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 17፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪዎችን ተጠቃሚ ያደረገው ብሔራዊ የታለመለት የነዳጅ ድጎማው አተገባበር በጅምር ደረጃ በመልካም ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑ ተመላከተ፡፡

የብሔራዊ የታለመለት የነዳጅ ድጎማ አስተባባሪ ኮሚቴ የአፈፃፀም ሪፖርት ግምገማ አካሂዷል፡፡

የታለመለት የነዳጅ ድጎማ ተግባራዊ ከመሆኑ አስቀድሞ ሰፊ የግንዛቤ መድረኮች መዘጋጀታቸው፣ የክልልና ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮዎች የድጎማው ተጠቃሚ የሚሆኑ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪዎችን የመለየት ስራን በተሳካ ሁኔታ መፈፀማቸው፣ ከባለሦስት እግር (ባጃጅ) ጀምሮ እስከ ሀገር አቋራጭ አውቶብስ ድረስ ባሉ የተለያዩ ሰባት ምድቦች የተቀመጡ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች አገልግሎቱን እያገኙ ነው ተብሏል፡፡

ከ615 በላይ ነዳጅ ማደያዎች በቂ ግንዛቤ ተፈጥሮላቸው አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኝ እንዲሁም የበለፀገው መተግበሪያ በሙከራ ተረጋግጦ ውጤታማነቱ የታየበትና ተጠቃሚዎች በቀላሉ መላመዳቸውም በጥንካሬ ተነስቷል፡፡

የክልሎችና ከተማ አስተዳድሮች ትራንስፖርት ቢሮዎች ምዝገባ አድርገው መረጃቸውን ወደ ማዕከል ከላኩት ከ186 ሺህ በላይ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪዎች መካከል 72 ከመቶ ያህሉ በቴሌ ብር ምዝገባ አድርገው የተሟላ መረጃ መያዙና አገልግሎቱን ለማግኘት ብቁ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

አንዳንድ አሽከርካሪዎች ምዝገባውን ባከናወኑበት ወቅት የሰጡት መረጃ በተለይ ስልክ ቁጥር ክፍተት የነበረበት በመሆኑ አገልግሎቱን ማግኘት አለመቻላቸው የተገለጸ ሲሆን ፥ እሱን ለማስተካከል በተደረገው ሂደት በነፃ የጥሪ ማዕከል 9719 ላይ የስራ ጫና ማሳደሩ ተመላክቷል፡፡

በመጨረሻም አስተባባሪ ኮሚቴው የታለመለት የነዳጅ ድጎማ ተግባራዊ መሆን ከጀመረበት ከሰኔ 29 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ባሉ ቀናት ያሉ ሂደቶች መልካም መሆናቸውን ተመልክቷል፡፡

በቀጣይ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በትኩረትና በላቀ አፈፃፀም መከናወን የሚገባቸውን ተግባራት በመለየት ስኬቱን ማስቀጠል እንደሚገባ ከመግባባት ላይ መደረሱን ከትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!