አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ ) ከ15 ዓመታት በኋላ አዲሷ ሴት የሕንድ ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት ድሮፓዲ ሙርሙ ቃለ መሐላ መፈጸማቸው ተገልጿል፡፡
ዛሬ በአገሪቱ መዲና ኒው ደልሂሊ በሚገኘው ማዕከላዊ የፓርላማ አዳራሽ ቃለመሐላ የፈጸሙት ድሮፓዲ ሙርሙ ÷ በፈረንጆቹ ከ2007 በተካሄደው አገር አቀፍ ምርጫ ሕንድን የመምራት ዕድል ካገኙት የመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዚዳንት ፕራቲባ ፓቲል ቀጥሎ ሀገር ለመምራት ዕድል ያገኙ ሁለተኛዋ ሴት ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡
“ናሽናል ዴሞክራቲክ አሊያንስ” ከተሰኘው የሕንድ ገዢ ፓርቲ የተገኙት ድሮፓዲ ሙርሙ አሸንፈው ሀገር ለመምራት የበቁት በሦስተኛው ዙር የድምጽ ቆጠራ ከጠቅላላው መራጭ ከ50 በመቶ በላይ ድምጽ በማግኘታቸው መሆኑም ተመልክቷል፡፡
ከሕንድ ምሥራቃዊ ኦዲሻ ግዛት የተገኙት ፕሬዚዳንት ሙርሙ የመንግስት ሥራ የጀመሩት በመምህርነት መሆም የተጠቆመ ሲሆን የፖለቲካውን ዓለም በፈረንጆቹ 1997 ተቀላቅለዋል፡፡
በፖለቲካው የመሪነት ድርሻቸውን መወጣት የጀመሩት ደግሞ በፈረንጆቹ ከ2015 እስከ 2021 የመጀመሪያዋ ሴት የምሥራቅ ጃርክሃንድ ግዛትን አስተዳዳሪ በመሆን ነው ተብሏል፡፡
ፕሬዚዳንት ድሮፓዲ ሙርሙ ለመሪነት የበቁት በፈረንጆቹ ሐምሌ18 በተካሄደው ምርጫ ከተፎካካሪ ፓርቲ የተወዳደሩትን ዕጩ ያሽዋንት ሲንሃንን በማሸነፍ መሆኑን ሲጂቲ ኤን ዘግቧል፡፡
ተፎካካሪያቸው ያሽዋንት ሲንሃን ከፈረንጆቹ 1990 እስከ 1991 የሀገሪቱ ገንዘብ ሚኒስትር በመሆን አገልግለዋል፡፡