የሀገር ውስጥ ዜና

የተፎካካሪ ፓርቲዎች የክልሉን ህዝቦች ሰላም በማስጠበቅ ረገድ ሚናቸው የላቀ ነው – አቶ ርስቱ ይርዳ

By Meseret Awoke

July 25, 2022

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የተፎካካሪ ፓርቲዎች የክልሉን ህዝቦች ሰላም በማስጠበቅ ረገድ ሚናቸው የላቀ መሆኑን የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳ ገለጹ፡፡

በደቡብ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በ2014 በጀት ዓመት አፈጻጸም ላይ በሐዋሳ ከተማ ውይይት እያካሔዱ ሲሆን ÷ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህ ወቅት የተፎካካሪ ፓርቲዎች መጠናከር ለገዢው ፓርቲ የጥንካሬ ምንጭ ናቸው ብለዋል።

የተፎካካሪ ፓርቲዎች የክልሉን ህዝቦች ሰላም በማስጠበቅ ረገድ ሚናቸው የላቀ መሆኑን ገልጸውም ፥ የዴሞክራሲ ባህልን በማዳበር ለሀገር እድገት በጋራ መስራት ይገባል ነው ያሉት፡፡

ከዚህ ቀደም ተፎካካሪ ፓርቲዎች በጠላትነት ሲፈረጁ እንደነበር አውስተው ፥ አሁን ባለው የዴሞክራሲ ስርዓት ገዢው ፓርቲ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን በኃላፊነት ደረጃ ማሳተፉን በአብነት ጠቅሰዋል።

ይህም በኢትዮጵያ በሚካሔዱ ሁሉን አቀፍ ስራዎች በትብብር ለመስራት ያለውን ቁርጠኝነት እንደሚያመላክትም ተናግረዋል አቶ ርስቱ።

ተፎካካሪ ፓርቲዎች በልማትና በመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ላይ የሚታዩ ጉድለቶችን በመለየት ችግሮች እንዲታረሙ ማድረግ ይኖርባቸዋልም ነው ያሉት።

እንደ ርዕሰ መስተዳድሩ ገለጻ ፥ በክልሉ የሚነሱ የአደረጃጀት ጥያቄዎች ሰላማዊ በሆነ መንገድ መፍታት እንዲቻል የላቀ አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚገባም ጠቁመዋል።

በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን የክልሉ መንግስት የበጀት እና የሎጂስቲክስ ድጋፍ እንደሚያደርግም አስረድተዋል።

የክልሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክርቤት ሰብሳቢ ወይዘሮ ፀዳለች ሚካኤል የምክር ቤቱን የ2014 በጀት ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት ፥ ምክር ቤቱ የተቋቋመለትን ዓላማ ለማሳካት የተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራዎችን ማከናወኑን ጠቁመዋል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!