ዓለምአቀፋዊ ዜና

ቻይና የአፍሪካና የቻይና የሰላምና ደኅንነት ትብብር እንዲጠናከር ጥሪ አቀረበች

By Alemayehu Geremew

July 26, 2022

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የቻይና-አፍሪካ የሰላም እና ደኅንነት ትብብር እንዲጠናከር የቻይና መከላከያ ሚኒስትር ዌይ ፌንጌ ጥሪ አቅርበዋል።

ሚኒስትሩ በቪዲዮ በተካሄደው የቻይና-አፍሪካ የሚኒስትሮች ፎረም ስብሰባ የቻይና ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ በጽሑፍ ያስተላለፉትን መልዕክት ያቀረቡ ሲሆን ÷ የቻይና-አፍሪካን የጋራ ማኅበረሰብ መገንባት ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው መግለጻቸውን እና ይህንንም ዕውን ለማድረግ ያላቸውን ጽኑ ፍላጎት ማስታወቃቸውን ተናግረዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ በመልዕክታቸው ቻይና እና አፍሪካ የመሰረቱትን ጠንካራ ስትራቴጂያዊ ግንኙነት ማስቀጠል እንዳለባቸውና ግንኙነታቸው በመሳሪያ እና በቴክኖሎጂ ትብብር ፣ በጋራ የባሕር ኃይል ልምምዶች እና ሥልጠናዎች እንዲሁም ሙያዊ ተሞክሮዎችን በማስፋት ላይ መሆን እንዳለበት ነው የጠቆሙት።

በበይነ-መረብ ትናንት በተካሄደው ሁለተኛው የቻይና-አፍሪካ የሰላም እና የደኅንነት ፎረም የሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ የተሳተፉት የአፍሪካ ሀገራት ተወካዮች ÷ ቻይና ለአፍሪካ ሰላም፥ ልማት እና ደኅንነት የምታደርገውን ድጋፍ ያደነቁ ሲሆን በቀጣይ በቀረበው ሀሳብ ላይ በትብብር ለመስራት ያላቸውን ፍላጎትም ነው የገለጹት፡፡

በቻይና- አፍሪካ የሚኒስትሮች ፎረም ስብሰባ ላይ የአፍሪካ ኅብረትንና የአፍሪካ ሀገራትን የሚወክሉ 50 በሚኒስትር ደረጃ የሚገኙ ባለሥልጣናት እና ከፍተኛ ተወካዮች መሳተፋቸውን ሽንዋ ዘግቧል።