የሀገር ውስጥ ዜና

ትብብር እና አንድነታችን የድል ብስራታችን መሰረት ነው- ዶ/ር ይልቃል ከፋለ

By Melaku Gedif

July 28, 2022

ትብብር እና አንድነታችን የድል ብስራታችን መሰረት ነው- ዶ/ር ይልቃል ከፋለ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 21፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ትብብር እና አንድነታችን የድል ብስራታችን መሰረት ነው ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ገለጹ፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ÷ በ18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ላስመዘገቡት አንጸባራቂ ድል የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ዶክተር ይልቃል በመልዕክታቸው÷ኢትዮጵያን ያስቀደሙ ድንቅ አትሌቶቻችን በ18ኛው የኦሪጎን ዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለመላ ኢትዮጵያውያን ክብር፣ ኩራት እና ደስታን አብስረዋል ነው ያሉት፡፡

አትሌቶቹ ሀገራቸውን በዓለም መድረክ አስጠርተው በአሸናፊነትና በድል ተመልሰዋል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ ኢትዮጵያዊነት የድል አድራጊነት ተምሳሌት፣ አልበገር ባይነትና የአሸናፊነት ወኔ ነው ብለዋል።

የአትሌቶቻችን አሸናፊነት እና ድል አድራጊነትም ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ለኢትዮጵያ ክብር ተሰልፈው በዓለም አደባባይ ስሟንና ሰንደቋን ከፍ አድርገው፣ በድል ለተመለሱ ድንቅ አትሌቶቻችንና መላ ኢትዮጵያውያን በሙሉ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ፡፡