አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኮሙኒኬሽን እና ሚዲያ ዘርፍ ለሚሰሩና ለኅብረተሰቡ መረጃ ለማድረስ ሙያዊ ግዴታቸውን እየተወጡ ለሚገኙ ባለሙያዎች የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ምስጋና አቅርቧል።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ባስተላለፉት መልዕክት መሰረት “ኢትዮጵያ ታመስግን” በሚል መሪ ቃል የምስጋና መርሐ ግብር አካሂዷል፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ዶክተር ለገሰ ቱሉ እንደተናገሩት ÷ የተቋሙ ዋነኛ ዓላማ የመንግስትን ዕቅዶችና ተግባራት በተመለከተ ለኅብረተሰቡ ትክክለኛ መረጃ መስጠት ነው፡፡
በመሆኑ ይህ ተግባር እንዲሳካ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ የሚገኙትን የመገናኛ ብዙሃንና የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎችን እናመሰግናለን ብለዋል፡፡
የኅብረተሰቡን የመረጃ ጥያቄ ለመመለስ ሙያ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ለሚገኙ ጋዜጠኞች፣ የካሜራ ባለሙያዎች እንዲሁም የተቋማትና የክልል ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎችም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ሚኒስትሩ ÷ “ዓለም በፈተና ውስጥ ቢሆንም እንኳ ሕዝባችን በልቶ እንዲያድር ሌት ተቀን ለሚደክሙት አርሶአደሮች፣ የሀገራችን ድንበርና ሉዓላዊነት እያስከበሩ ለሚገኙት የጀግናው መከላከያ ሰራዊትና መላው የጸጥታ ኃይላችን አባላት፣ ትውልድን ለሚያንጹ መምህራን፣ ለጤና ባለሙያዎች፣ ለመንግስት ሰራተኞች፣ በግል ስራ ለተሰማሩ ዜጎችና በሌሎችም ዘርፎች ሀገራቸውን በቅንነት እያገለገሉ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን በሙሉ እናመሠግናለን” ብለዋል።
ከገጠመን ፈተና ይልቅ ያገኘነው ጥንካሬና በአብሮነታችን ያስመዘገብናቸው መልካም ነገሮች ለነገ ስኬታችን ስንቅ ይሆኑናል ያሉት ዶክተር ለገሰ÷ እያንዳንዱ ዜጋ ለሀገሩ በጎ በማሰብና በመስራት የተጀመሩት መልካም ነገሮች እንዲሳኩ በጋራ ልንቆም ይገባል ብለዋል፡፡
በመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የሚዲያ ግንኙነት ክትትልና መረጃ ማደራጃ ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ሰላማዊት ካሳ በበኩላቸው÷ የዛሬው ቀን ኢትዮጵያ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ሆኗ ፈተናዎችዋን ሁሉ እንድትሻገር ለረዳት ፈጣሪዋ ምስጋና የምታቀርብበት ነው ብለዋል፡፡
በሁሉም ሃይማኖቶች ሰዎች ፈጣሪያቸውን ሲያመሰግኑ ይውላሉና ዛሬም ኢትዮጵያን ጠብቆ ላቆያት ፈጣሪ፤ በተባበረ አብሮነት ፈተናን አብረው ለተጋፈጡና መስዋእትነትንም ለከፈሉ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም በእያንዳንዳችንም የህይወት ቆይታ በጎ የሰሩልንን ሰዎች የምናመሰግንበት ቀን ነው ብለዋል ሚኒስትር ዴኤታዋ።
በአገልግሎቱ የሕዝብ ግንኙነትና የተቋማት ክትትል ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ከበደ ዴሲሳ÷ አትሌቶቻችን ለአንድ ሃገር ሲሮጡ ሌሎች ልዩነታቸውን ትተው ኢትዮጵያን እንዳስቀደሙት ሁሉ እኛም ሁልጊዜ ኢትዮጵያን አስቀድመን ለሃገር ግንባታ በጋራ ልንሰራ ይገባል ብለዋል፡፡