የሀገር ውስጥ ዜና

በጋምቤላ ክልል በ2014 ዓ.ም በገበያ ተኮር የግብርና ምርቶች ልማትና በገቢ አሰባሰብ ላይ የተሻለ አፈፃፀም ተመዝግቧል- አቶ ኡሞድ ኡጁሉ

By Meseret Awoke

July 29, 2022

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ክልል በበጀት ዓመቱ በገበያ ተኮር የግብርና ምርቶች ልማትና በገቢ አሰባሰብ ላይ የተሻለ አፈፃፀም መመዝገቡን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ተናገሩ፡፡

የጋምቤላ ክልልምክር ቤት 6ኛ የምርጫ ጊዜ 1ኛ የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባዔ መካሄድ ጀምሯል፡፡

የክልሉ ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ወ/ሮ ባንችየሁ ደንገታ በጉባዔው መክፈቻ ባደረጉት ንግግር ፥ የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር እቅዶችን ለማሳካት ሁሉም በአንድነት ሊሠራ ይገባል ብለዋል፡፡

ሙስናና ብልሹ አሠራሮችን በመታገል የተጀመረውን የልማትና የብልጽግና ጉዞ ዳር ለማድረስ እንዲሁም ቁልፍ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ምላሽ ለመስጠት የምክር ቤቱ አባላት በትኩረት እንዲሠሩ አሳስበዋል፡፡

በጉባዔው÷ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ የ2014 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት አቅርበዋል፡፡

በሪፖርቱም÷ በጋምቤላ ከተማ አሸባሪው ሸኔና የጋነግ ቡድኖች ሊፈጽሙት የነበረው የሽብር ጥቃት መክሸፉን ገልጸዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ በገበያ ተኮር የግብርና ምርቶች ልማት የተሻለ አፈፃፀም መመዝገቡን ጠቁመው÷ በ2014 ዓ.ም 30 ሺህ 582 ቶን የቡና ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ÷ 35 ሺህ 873 ቶን ተሰብስቧል ብለዋል፡፡

የገቢ አቅም በማሳደግ ረገድ የተሻለ አፈጻጸም እንደነበር ገልጸው÷ በበጀት ዓመቱ 1 ቢሊየን 167 ሚሊየን 31 ሺህ 427 ብር ለመሰብሰበ ታቅዶ 1 ቢሊየን 360 ሚሊየን 718 ሺህ 893 ብር መሰብሰቡን ተናግረዋል። ይህም ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ403 ሚሊየን 902 ሺህ 600 ብር ብልጫ እንዳለው አመላክተዋል፡፡

የኢንቨስትመንት ልማትን ከማሳደግ አኳያ÷ በግብርና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ለ268 ባለሃብቶች አዲስ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ለመስጠት ታቅዶ ከዕቅድ በላይ 3 ቢሊየን 534 ሚሊየን 579 ሺህ 834 ብር ካፒታል ላስመዘገቡ ለ302 ባለሃብቶች ፈቃድ መሰጠቱ በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

በበጀት ዓመቱ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ 1 ሺህ 600 ኪሎ ግራም የተጣራ ወርቅ ለማስገባት ታቅዶ÷ 1 ሺህ 206 ኪሎ ግራም የተጣራ ወርቅ ማስገባት እንደተቻለ ርዕሰ መስተዳድሩ በሪፖርታቸው አመላክተዋል፡፡

በሌሎች በትምህርትና በጤና ዘርፎች አበረታች ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቁመው÷ የግንባታ ተቋራጮች የማስፈፀም አቅም ማነስ፣ ፕሮጀክቶች ተጀምረው ያለመጠናቀቅና የጦር መሳሪያ ዝውውር መበራከት እንደ ችግር ተነስተዋል።

ጉባዔው በሦስት ቀን ቆይታው÷ የክልሉን የ2014 የልማትና መልካም አስተዳደር ዕቅድ፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት እና የዋና ኦዲት መስሪያ ቤት ሪፖርት አዳምጦ እንደሚያጸድቅ ይጠበቃል፡፡

እንዲሁም የ2015 በጀት ዓመት የልማትና የመልካም አስተዳደር እቅድ፣ የማስፈፀሚያ በጀት፣ የተለያዩ ረቂቅ አዋጆችን ጨምሮ የተለያዩ ውሳኔዎችን እንደሚያሳልፍ የክልሉ ፕሬስ ሴክሬታሪያት መረጃ ያመላክታል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!