የሀገር ውስጥ ዜና

የኤሌክትሪክ አገልግሎት የሥነ-ምግባር ጥሰት ፈጽመዋል ባላቸው 120 አመራሮችና ሠራተኞች ላይ እርምጃ ወሰደ

By Shambel Mihret

July 29, 2022

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተገናኘ ብልሹ አሰራርና የሥነ-ምግባር ጥሰት ሲፈጽሙ ተገኝተዋል በተባሉ 120 አመራሮችና ሠራተኞች ላይ የተለያዩ እርምጃዎች እንደተወሰዱባቸው ተገለጸ፡፡

የተቋሙ የሥነ ምግባርና ፀረ -ሙስና ዳይሬክተር አቶ ህብረወርቅ ይመኑ እንዳስታወቁት ፥ እርምጃው የተወሰደው በአገልግሎት አሰጣጥ ወቅት ከደንበኞች በቀረበ ቅሬታ መሰረት ነው፡፡

በ2014 በጀት ዓመት የግልጽነትንና ተጠያቂነትን ስርዓት ከጊዜ ወደ ጊዜ ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት ዳይሬክተሩ ፥ ተገልጋዮች ሀሳባቸውንና ጥቆማዎችን ለማቅረብ የሚችሉበትን ምቹ ሁኔታ በመፍጠር በበጀት ዓመቱ 145 ጥቆማዎችን በመቀበል የማጣራት ሥራ መሰራቱን  ነው የገለጹት፡፡

በአገልግሎት አሰጣጥ የቀረቡ ጥቆማዎችን መሰረት በማድረግ 120 አመራሮችና ሰራተኞች ላይ የተለያዩ አስተዳደራዊ እርምጃ የተወሰደ ሲሆን ፥ ቀሪ 101 የሚሆኑት ጥፋተኞች ደግሞ ጉዳያቸው በተቋሙ የዲሲፕሊን ኮሚቴ በመታየት ላይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ከደንበኞች ቀርበው በተጣሩ ጥቆማዎች መሰረት የታዩ የብልሹ አሰራር መገላጫዎች መካከል በሕገ ወጥ መንገድ ቆጣሪ ማስገባት፣ ጉቦ መጠየቅ፣ ደንበኛን ማጉላላት፣ ያለበቂ ምክንያት ስራን ማዘግየት፣ ለአስቸኳይ ጥገና ሥራ ደንበኞች ገንዘብ አዋጠው እንዲከፍሉ ማስገደድ፣ ያለደረሰኝ የቆጣሪ ማስገቢያ ክፍያ መቀበል እና ሌሎች መሰል ብልሹ አሰራሮች መሆናቸውን ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡

በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ ከደንበኞች የመጡትን ጥቆማዎች ጨምሮ ተቋሙ ያስቀመጠውን የውስጥ አሰራር ስርዓት ያላከበሩና የሥነ-ምግባር ጥሰት በፈፀሙ በድምሩ 1 ሺህ 50 አመራሮችና ሠራተኞች ላይ የተለያዩ አስተዳደራዊ እርምጃዎች መወሰዱንም ገልፀዋል፡፡

አስተዳደራዊ እርምጃው የተወሰደው በተቋሙ ህብረት ስምምነትና በማኔጅመንት መተዳደሪያ ደንብ መሰረት መሆኑን የገለፁት ዳይሬክተሩ ፥ የቃል ማስጠንቀቂያ 27፣ የጸሑፍ ማስጠንቀቂያ 356፣ የደመወዝ/ገንዘብ ቅጣት 568፣ ከቦታ ማንሳት 24 እና ስንብት 75 እርምጃዎች ተወስደዋል ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፡፡

ደንበኞች ብልሹ አሰራሮችን በማጋለጥና መብታቸውን በሕጋዊ መንገድ በማስከበር የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ጥሪ ማቅረባቸውን ከአገልግሎቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡