አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የእስልምና እምነት ተከታዮች “ኢትዮጵያ ታመስግን” የምስጋና መርሐ ግብር ዛሬ በታላቁ አንዋር መስጅድ አካሂደዋል፡፡
መርሐ ግብሩ የተካሄደው የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የጁመዓ ሰላትን ተከትሎ የምስጋና መርሐ ግብሩ እንዲደረግ ባስታወቀው መሰረት ነው ተብሏል።
የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በዛሬው ቀን በመላው ኢትዮጵያ ያሉ የእስልምና እምነት ተከታዮች ከጁመዓህ ስግደት በኋላ የሶስት ደቂቃ የምስጋና ጸሎት እንዲደረግ ጥሪ ማስተለፉም ይታወቃል።
በመርሐ ግብሩ ላይ ለሀገር ፣ ለሰላም፣ ለመሪዎች እንዲሁም ለኢትዮጵያ ጸሎት እና ልመና ተደርጓል።
በጉባኤው ጥሪ መሰረት ነገ የአድቬንቲስት እምነት ተከታዮች እንዲሁም ከነገ በስቲያ የኦርቶዶክስ ፣የካቶሊክ እምነትና የፕሮቴስታንት እምነቶች ከቅዳሴና መርሐ ግብሮቻቸው በኋላ ለፈጣሪ ምስጋና እንደሚያቀርቡ መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል፡፡