የሀገር ውስጥ ዜና

የሐረሪ ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባዔውን ማካሄድ ጀመረ

By Shambel Mihret

August 02, 2022

የሐረሪ ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባዔውን ማካሄድ ጀመረ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሐረሪ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 1ኛ ዓመት 2ኛ መደበኛ ጉባዔውን ዛሬ ማካሄድ ጀምሯል።

በጉባዔው የክልሉ መንግስት የ2014 የሥራ አፈፃፀም ሪፖርት በርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ቀርቧል፡፡

ርዕሰ-መስተዳድሩ በሪፖርታቸው የሐረሪ ክልል በ2014 በጀት ዓመት 2 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ገቢ ለመሰብሰብ አቅዶ 3 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር መሰብሰቡን አመላክተዋል፡፡

ክልሉ በውስጥ አቅም 1 ነጥብ 06 ቢሊየን ብር ገቢ ለመሰብሰብ አቅዶ፥  1 ነጥብ 13 ቢሊየን ብር ገቢ በመሰብሰብ ከዕቅዱ በላይ ማሳካት መቻሉንም ነው የገለጹት፡፡

ይህም እንደ መልካም ስኬት የሚታይ መሆኑን አቶ ኦርዲን ተናግረዋል፡፡

በግብርና ልማት ዘርፍ ምርትና ምርታማትን ለማሳደግ የተለያዩ ሥራዎች መሰራታቸው አቶ ኦርዲን በተጨማሪ ያመላከቱ ሲሆን፥ በ2014 የምርት ዘመን በአጠቃላይ 11 ሺህ 839 ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን ታቅዶ 11 ሺህ 565 ሄክታር መሬት መሸፈን መቻሉንም ገልጸዋል፡፡

በቀጣይ የክልሉ የዋናው ኦዲተር መስሪያ ቤት እና የጠቅላይ ፍርድ ቤት የ2014 እቅድ አፈፃፀም የ2015 በጀት ዓመት ሪፖርትና ዕቅድ እንዲሁም የክልሉ መስተዳድር የ2015 ረቂቅ በጀት አዋጅ ቀርቦ ውይይት ተካሄዶበት ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።

ምክር ቤቱ የሐረር ከተማ መዋቅራዊ ፕላን ፣ ረቂቅ አዋጆች እና ሹመቶች ላይም በመምከርም ውሳኔዎች እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል፡፡

ጉባዔው ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት የሚቆይ መሆኑ ታውቋል፡፡

በቲያ ኑሬ

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

 

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

 

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!