የሀገር ውስጥ ዜና

የተተከሉ ችግኞችን በህብረት በመንከባከብ ምቹና ተስማሚ የሆነች ኢትዮጵያን መገንባት ያስፈልጋል – ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ

By Shambel Mihret

August 03, 2022

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የተጀመረውን የአረጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከግብ ለማድረስ የተተከሉ ችግኞችን በህብረት በመንከባከብ ምቹና ተስማሚ የሆነች ኢትዮጵያን መገንባት እንደሚያስፈልግ የፍትህ ሚኒስትር ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ ገለጹ፡፡

የፍትህ ሚኒስትር ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ በመተከል ዞን ግልገል በለስ ከተማ ተገኝተው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር አከናውነዋል፡፡

ዶክተር ጊዲዮን ጢሞቲዎስ በዚሁ ወቅት  እንደገለጹት÷ ቀጠናው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መገኛ በመሆኑ ይህን ሊመጥን የሚችል የአካባቢ ጥበቃ ስራ ከማከናወን በተጨማሪ የተገኘው ሰላም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሁሉም መረባረብ አለበት፡፡

በዞኑ ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ሃብት ማልማት እና የዜጎችን ሁሉን አቀፍ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚቻለው ሰላም ሲሰፍን በመሆኑ ይሄን ማስቀጠል የሁሉም ዜጋ ድርሻ ነው ብለዋል።

በግልገል በለስ ከተማ በተካሄደው የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር የፍትህ ሚኒስቴር ሰራተኞችን ጨምሮ የክልልና የዞን ከፍተኛ አመራሮች መሳተፋቸውን ከመተከል ዞን ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በሌላ በኩል÷ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ኢንስቲትዩት እንዲሁም የአፋር ክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በሠመራ ከተማ ችግኝ የተከሉ ሲሆን በመርሐ ግብሩ ላይ÷ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ፣ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታዎች አቶ አሰግድ ጌታቸው እና ወ/ሮ ነቢሃ መሀመድ መሳተፋቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!