ዓለምአቀፋዊ ዜና

የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ባለቤት በኮሮና ቫይረስ ተያዙ

By Meseret Demissu

March 13, 2020

አዲስ አበባ፣መጋቢት 4፣ 2012(ኤፍ.ቢ.ሲ) የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ ባለቤት ሶፊ ትሩዶ በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው ተረጋገጠ።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለቤት ከለንደን ከተመለሱ በኋላ የቫይረሱ ምልክት ባለፈው ረቡዕ ምሽት ላይ እንደታየባቸው ተገልጿል።

በተደረገላቸው ምርመራም ቫይረሱ የተገኘባቸው ሲሆን፥ ለብቻቸው እንዲቆዩ መደረጉም ነው የተገለጸው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ትሩዶ የቫይረሱ ምልክት ባይታይባቸውም ራሳቸውን አግልለው ስራቸውን ይሰራሉ ተብሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ትሩዶ በትዊተር ገፃቸው ባሰፈሩት ፅሁፍ እስከተወሰነ ጊዜ ድረስ ከህብረተሰቡ ጋር ያለኝን ግንኙነት እንድገድብ ምክር ተሰጥቶኛል ብለዋል።

በአሁኑ ጊዜ በካናዳ 103 ሰዎች በኮሮና ቫይረስ መጠቃታቸው ተነግሯል።

በሌላ በኩል የብራዚል ፕሬዚዳንት ጃየር ቦልሶናሮ ረዳት ፋቢዮ ዋጂንጋርተን በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው ተረጋግጧል።

ባለስልጣኑ ባለፈው ቅዳሜ በአሜሪካ ፍሎሪዳ ከፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ለስራ ስብሰባ መገናኘታቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ።

የፕሬዚዳንት ቦልሶናሮ ልጅ ኤድዋርዶ ቫይረሱ በረዳታቸው ላይ ከተገኘ በኋላ አባቱ  ምርመራ ማድረጋቸውንና ውጤቱን በመጠባበቅ ላይ  መሆናቸውን ገልጿል።

የኮሮና ቫይረስ ስርጭት የስፖርቱን ዓለም ያዳረሰ ሲሆን፥ የአርሰናሉ አሰልጣኝ ሚካኤል አርቴታ እና የቼልሲው ተጫዋች ሀድሰን ኦዶይ የቫይረሱ ተጠቂዎች ሆነዋል።

ከዚህ ባለፈም የማንቼስተር ሲቲው ተከላካይ በርናንድ ሜንዲ የቤተሰቡ አባላት ሆስፒታል በተደረገላቸው ምርመራ የቫይረሱን ምልክት ማሳየታቸውን ተከትሎ ራሱን ማግለሉም ተሰምቷል።

በተጨማሪም ስማቸው ያልተጠቀሰ ሶስት የሌሲስተር ሲቲ ተጫዋቾች የቫይረሱን ምልክት በማሳየታቸው ራሳቸውን አግልለዋል።

ምንጭ፦ ቢ.ቢ.ሲ እና አልጀዚራ

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ! https://t.me/fanatelevision