አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 29፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግስት በጀመረው የአስር ዓመት የልማት ዕቅድ ለግብርና ዘርፍ ቅድሚያ ሰጥቶ እየሰራ ነው ሲሉ በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ተናገሩ፡፡
አምባሳደሩ ከቻይና የውጭ ኢኮኖሚያዊ ልማት ትብብር ማዕከል ምክትል ዳይሬክተር ጄኔራል ሊን ሁይፋንግ ጋር በግብርና ዘርፍ በትብብር ለመስራት የሚያስችል ውይይት አድርገዋል፡፡
በውይይቱ ወቅት አምባሳደር ተሾመ ፥ የኢትዮጵያ መንግስት በጀመረው የአስር ዓመት የልማት ዕቅድ ለግብርና ዘርፍ ልማት ቅድሚያ ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የግብርናው ዘርፍ ልማት ፕሮግራም በአፍሪካ – ቻይና የልማት ትብብር ማዕቀፍ ልዩ ትኩረት ከተሰጣቸው ዘጠኝ ዋና ዋና የልማት ግቦች መካከል አንደኛው መሆኑን ጠቁመዋል።
ሊን ሁይፋንግ በበኩላቸው ፥ ቻይና በግብርና ኢንቨስትመንት፣ በቴክኒክ ድጋፍ፣ በምርት ማስተዋወቅ ረገድ ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ ትቀጥላለች ማለታቸውን በቻይና የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡