የሀገር ውስጥ ዜና

በደቡብ ምዕራብ ክልል አልፎ አልፎ የሚስተዋለውን የጸጥታ ስጋት ለመቆጣጠር የተሰራው ስራ አንጻራዊ ሰላም አምጥቷል- ዶ/ር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ

By Shambel Mihret

August 06, 2022

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በድንበር አካባቢ አልፎ አልፎ የሚስተዋለውን የጸጥታ ስጋት ለመቆጣጠር ከሕብረተሰቡ ጋር የተሰራው ስራ አንጻራዊ ሰላም ማምጣቱን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ገለጹ፡፡

ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ክልሉ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ በተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት ዙሪያ  መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸውም÷በክልሉ ከ1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 38 ባለሀብቶች በግብርና፣ በአገልግሎት ዘርፍና በሌሎች የኢንቨስትመንት አማራጮች ወደ ስራ እንዲገቡ መደረጉን ገልጸዋል።

በግብርና ዘርፍ በበልግና በመኸር እርሻ 548 ሺህ ሄክታር መሬት በማልማት ከ55 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን ገልጸው÷ለቡና ምርት ልዩ ትኩረት በመስጠት ከ64 ሺህ 400 ቶን በላይ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ማቅረብ መቻሉን ጠቁመዋል።

በበጀት ዓመቱ በ7 ወራት 3 ቢሊየን 17 ሚሊየን ብር ገቢ መሰብሰቡን፣ ከ195 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል መፈጠሩን እንዲሁም  የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነቱን ለማቃለል በማህበራት በኩል የተለያዩ የግብርና ምርቶችን የማቅረብና ህገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴን የመከላከል ስራ መሰራቱን ገልጸዋል።

በጸጥታ ዘርፍ አልፎ አልፎ የሚስተዋለውን የጸጥታ ስጋትና በአርብቶ አደሮች አካባቢ ከጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ጋር በተያያዘ የሚከሰት ግጭትን ለመቆጣጠርና ለመከላከል ከሕብረተሰቡ ጋር በመወያየት የተሰራው ስራ አንጻራዊ ሰላም ማምጣት ማስቻሉን አስረድተዋል።

ክልሉ ሲመሰረት በህዝቦች መፈቃቀድና መከባበር ብዝሃ ዋና ከተሞች እንዲኖሩት መደረጉን ጠቅሰው÷ ከክልሉ ነዋሪ ጋር በመመካከርና በህገ መንግስቱ በማስቀመጥ የፖለቲካና የአስተዳር ዘርፍ በቦንጋ ማዕከል እንዲሆን መወሰኑን ገልጸዋል።

የህግ አውጪውን በተርጫ ማዕከል፣ የዳኝነት አካሉን በሚዛን አማንና የብሔረሰቦች ምክር ቤት በቴፒ ከተማ በማድረግ ክልሉ 4 ብዝሃ ከተሞች እንዲኖሩት ተወስኖ ወደ ስራ መገባት መቻሉን ተናግረዋል።

በብዝሃ ዋና ከተማነት ከተለዩት ከተሞች ውጭ የአመያና የጀሙ ከተሞችም ተያይዞ ለማደግና ለመልማት በተቀመጠው መርሕ መሰረት ከተጠሪ ተቋማት ድልድል ተደራሽ እንደሚደረጉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!