አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) 42 ባለሀብቶችና የግል አልሚዎችን ወደ ቡልቡላ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለመግባት ቃል መግባታቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የቡልቡላ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ የመሠረተ ልማት ግንባታው ተጠናቆ ባለሃብቶችና የግል አልሚዎችን በተሻለ ደረጃ ለመጥቀም ሙሉ ዝግጅቱን ማጠናቀቁንና 135 ባለሀብቶችን የማስተናገድ አቅም እንዳለው ተገልጿል፡፡
በኢንዱስትሪ ፓርኩም ወደ 42 የሚጠጉ ባለሃብቶችና የግል አልሚዎች ለመግባታ ቃል ገብተዋል፡፡
የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል÷ መንግሥት የአገሪቷን የኢኮኖሚ ሽግግር እውን ለማድረግ ባለፉት ሦስት ዓመታት የቡልቡላ፣ የይርጋለም፣ የቡሬ የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታቸውን አጠናቀው ወደ ስራ መግባታቸውን ገልጸው ኢንቨስት የሚያደርጉ ባለሃብቶችም እየተመዘገቡ መሆኑን አንስተዋል።
እስካሁን በሶስቱ ፓርኮቹ ውስጥ 94 ባለሃብቶች መመዝገባቸውን ጠቁመው ከተመዘገቡት ውስጥ ስድስት ባለሃብቶች ማምረት መጀመራቸውን አስታውቀዋል።
በግብርና ማቀነባበሪያ ፓርኮቹ ውስጥ ተመዝግበው ሥራ ከጀመሩ ባለሃብቶች ውስጥ ሦስቱ ወደ ውጭ መላክ የጀመሩ ሲሆን÷ በሁለት ዓመት ውስጥ 16 ነጥብ 2 ሚሊየን ዶላር ከውጭ ንግድ ገቢ መገኘቱን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ሥራ በመጀመራቸው 144 ሺህ አነስተኛ አርሶ አደሮች ምርታቸውን እንዲያቀርቡ ማስቻሉን የጠቀሱት ሚኒስትሩ ግብርና ማቀነባበሪያዎቹ ለቴክኖሎጂ ሽግግር፣ ለምርት ጥራት ማደግ ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ገልፀዋል።
መንግሥት ከፍተኛ ወጪ በማውጣት ባለሀብቶች ላይ የሚፈጠረውን ጫና ለማቃለል እየሰራ ነው፤ ባለሃብቶችም እድሉን በመጠቀም ኢንቨስት ማድረግ እንደሚኖርባቸው አመልክተዋል።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!