የሀገር ውስጥ ዜና

ከተሞችን አረንጓዴ ውብና ጽዱ በማድረግ ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ እየተሰራ ነው – ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ

By Shambel Mihret

August 09, 2022

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ከተሞችን አረንጓዴ ውብና ጽዱ በማድረግ ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትሯ ጫልቱ ሳኒ ገለጹ።

የከተሞችን ቆሻሻ ወደ ሌሎች ምርቶች ለመቀየር የሚያገለግል የመፍጫ ማሽን የድጋፍ ርክክብ መርሐ ግብር እየተካሄደ ነው፡፡

ከተሞች እያደጉ ከመምጣታቸው ጋር ተያይዞ ከተሞችን ውብና ጽዱ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ ገልጸዋል፡፡

የተለያዩ ከተሞች ደረቅ ቆሻሻን የማስወገድ ስራ እያከናወኑ ቢሆንም አሁንም ግን ትልቅ ስራ የሚጠይቅ ነው ተብሏል።

ቆሻሻ የገንዘብ ምንጭ የሆነበትና የስራ እድልን የፈጠረ ሃብት መሆኑን ያሳዩ ከተሞች እንዳሉ ሁሉ አሁንም ግን በትኩረት ሊሰራትበት እንደሚገባ መገንዘብ ይገባልም ነው ያሉት ሚኒስትሯ።

የከተማ ነዋሪም ቆሻሻን በወጉ ለይቶ በማስወገድ ሃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በዚህ መሰረትም የከተሞችን ቆሻሻ በተለይም የፕላስቲክ ጠርሙሶችን በመፍጨት ወደ ሌሎች ምርቶች የሚቀይር የመፍጫ ማሽን ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ድጋፍ ተደርጓል ብለዋል።

ለአምስት ከተሞች ብቻ የማሽን ድጋፍ ቢደረግም በቀጣይ ለሁሉም ከተሞች ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ድሬዳዋ፣ አዳማ፣ ባህርዳር፣ ቢሾፍቱ እና ሐዋሳ የማሽኑ ድጋፍ የተደረገላቸው ከተሞች ናቸው።

በዛሬው የመጀመሪያ ዙር የማሽን ድጋፍ እድለኛ የሆኑ ከተሞች ማሽኖችን በተገቢው መንገድ ተግባር ላይ በማዋል ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

በይስማው አደራው

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!