አዲስ አበባ፣ መጋቢት 5፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኦሮሚያ ክልል ምእራብ ሸዋ ዞን ለሚገነባው የመከላከያ ካምፕ በዛሬው እለት የመሰረተ ድንጋይ ተቀመጠ።
በመከላከያ መሃንዲስ ዋና መምሪያ የሚገነባው የሻለቃ መኖሪያ ካምፑ በኦሮሚያ ክልል ምእራብ ሸዋ ዞን ደንዲ ወረዳ አዋሽ ቦሌ ቀበሌ የሚገነባ መሆኑንም የምእራብ ሸዋ ዞን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታውቀውል።
የመሰረተ ድንጋዩንም የመከላከያ መሃንዲስ ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄነራል ጌታቸው ጉዲና፣ ሜጀር ጄነራል ከፍያለው አምዴ፣ ሜጀር ጄነራል ብርሃኑ በቀለ እና የምእራብ ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ድሪርሳ ዋቁማ አስቀምጠዋል።
የመከላከያ መሃንዲስ ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄነራል ጌታቸው ጉዲና በዚሁ ወቅት፥ የሻለቃ መኖሪያ ካምፑ መገንባት ለአካባቢው ልማት፣ ኢኮኖሚ እና ሰላም መስፈን ጠቀሜታ አለው ብለዋል።
በ60 ሚሊየን ብር በ12 ሄክታር መሬት ላይ የሚካሄደው የካምፑ ግንባታ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚጀመር መሆኑንም አስታውቀዋል።
የምእራብ ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ድሪርሳ ዋቁማ በበኩላቸው፥ የካምፑ ግንባታ የአካባቢውን ሰላም ከማስጠበቅ በተጨማሪ የስራ እድልን ከመፍጠር አንጻር ጠቀሜታ እንዳለው ገልፀዋል።
የአካባቢው ነዋሪዎችም ይህንን በመረዳት የመጣላቸውን ልማት መንከባከብ እንደሚገባቸውም ጥሪ አቅርበዋል።