አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 14፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በግጭት መከላከል ዙሪያ የተሰጠው ስልጠና በአፍሪካ እና በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮን በብቃት ለመወጣት ክህሎት ያስጨበጠ መሆኑን በመከላከያ ሰላም ማስከበር ማዕከል የዓለም አቀፍ ሰላም ማስከበር ማሰልጠኛ ተቋም አዛዥ ብ/ጄኔራል ሰብስቤ ዱባ ገለጹ፡፡
በመከላከያ ሰላም ማስከበር ማዕከል ዓለም አቀፍ ሰላም ማስከበር ማሰልጠኛ ተቋም የጃፓን መንግስት እና የተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት በጋራ ተዘጋጅቶ በድህረ ግጭት ማገገም ዙሪያ ሲሰጥ የቆየው ስልጠና ተጠናቋል፡፡
ኢትዮጵያን ጨምሮ፣ ከናይጀሪያ፣ ከኮንጎ፣ ከኤርትራ፣ ከሶማሊያ፣ ከጅቡቲ፣ ከደቡብ ሱዳን እና ከኡጋዳ የሠራዊት እና የፖሊስ አባላት እንዲሁም ከሲቪል ማህበረሰብ የተውጣጡ አባላት በስልጠናው ተሳትፈዋል።
ብ/ጄኔራል ሰብስቤ÷ ስልጠናው በአፍሪካ ሰላም እና ፀጥታ እና በተባበሩት መንግሥታት ዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎችን በብቃት ለመወጣት ክህሎት ያስጨበጠ ነው ብለዋል፡፡
ሰልጣኞች በድህረ ግጭት የማገገም ሥራ፣ የግጭት መንስኤና ግጭቶች እንዴት እንደሚፈቱ ግንዛቤ እንዳገኙም ተጠቁሟል፡፡
በስልጠናው የተገኘውን ዕውቀት ሰልጣኞች ወደ ውጤት በመቀየር በተሰማሩበት መስክ ሁሉ የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት ይኖርባቸዋል ሲሉ ጄነራል መኮንኑ ማሳሰባቸውን ከመከላከያ ሠራዊት የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
በዓለም አቀፍ ሰላም ማስከበር ተቋም የጃፓን ከፍተኛ አማካሪ ሌ/ኮሌኔል ኡራካሜ ኑራሻ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት የሰላም ማስከበር ተሳትፎ በተለይም በምስራቅ አፍሪካ ሰላምን በማረጋጋት ከፍተኛ ሚና እየተጫወተች እንደምትገኝ ገልፀዋል፡፡