የሀገር ውስጥ ዜና

በአርብቶ አደር አካባቢዎች በቂ እርጥበትን በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚገባ ተጠቆመ

By Alemayehu Geremew

August 22, 2022

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች ከመደበኛው ወቅት ጋር የተቀራረበ የእርጥበት ሁኔታ ስለሚኖር ከወዲሁ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ መጠቀም እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሜቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አሳሰበ፡፡

እርጥበቱ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ የግጦሽ ሳር ልምላሜ እንዲሁም የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ የውኃ ምንጮችን በተሻለ ሁኔታ ለመጠቀም በጎ ሚና እንደሚኖረው አመላክቷል፡፡

የእርጥበት ሁኔታው በምሥራቅና ደቡብ ደጋማ ሥፍራዎችም አንጻራዊ መስፋፋት እንደሚያሳይ መረጃው ጠቁሟል፡፡

ከግብርና እንቅስቃሴ አንጻር በተለያየ የዕድገት ደረጃ ላይ የሚገኙ የመኸር ሰብሎችን የመከታተል ሥራዎች መከወን እንደሚያስችልም ገልጿል፡፡

በተሰጠው የአስራ አንድ ቀን የዓየር ሁኔታ ትንበያ መሠረት አልፎ አልፎ ከሚጠናከሩ የሚቲዎሮሎጂ ገፅታዎች ጋር ተያየዞ አንዳንድ አካባቢዎች ከባድ ዝናብ ሊኖራቸው እንደሚችል ተጠቁሟል።

በቀጣይነት ከሚጠበቀው እርጥበት ጋር ተያይዞ የአረም መሥፋፋትም ሆነ የተለያዩ የሠብል በሽታዎች ሊከሰቱ ስለሚችል አስፈላጊው ቅድመ-ጥንቃቄ እና ክትትል ከወዲሁ እንዲደረግም የሚመለከታቸውን አካላት አሳስቧል፡፡

በአንዳንድ አካባቢዎች የሚጠበቀው ከባድ ዝናብ የጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት ችግሮችን ሊያስከትል ስለሚችል ከወዲሁ ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ ነውም ብሏል፡፡

በሌላ በኩል በሰሜን ኢትዮጵያ ቆላማ አካባቢዎች የዕርጥበት ሁኔታቸው ቀስ በቀስ የመቀነስ አዝማሚያ የሚያሣይበት ጊዜ እንደሚሆን የኢትዮጵያ ሜቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት መረጃ አመላክቷል፡፡