ዓለምአቀፋዊ ዜና

ቻይና ከሩሲያ የምታስገባው የሃይል አቅርቦት መጠን ጭማሪ አሳየ

By Amele Demsew

August 23, 2022

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 17፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ቻይና ከሩሲያ የምትገበያየውን የሃይል አቅርቦት መጠን ከፍ ማድረጓ ተሰማ፡፡

ቤጂንግ ከመጋቢት ወር ጀምሮ ከሩሲያ ለተገበያየቻቸው የነዳጅ ድፍድፍ፣ የነዳጅ ዘይት፣ የጋዝ እና የድንጋይ ከሰል ምርቶች 35 ቢሊየን ዶላር ወጪ ማድረጓ ተሰምቷል፡፡

የሩሲያ ዩክሬን ግጭት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ምዕራባውያን በሞስኮ ላይ ከጣሉት ማዕቀብ በኋላ ከሩሲያ ወደ ቻይና የሚገቡ የሃይል አቅርቦት ምርቶች ከ75 በመቶ በላይ መጨመራቸውን የቻይናን የቅርብ ጊዜ የጉምሩክ አሃዞች በመጥቀስ ብሉምበርግ ዘግቧል።

እንደ መረጃው ከሆነ ከመጋቢት እስከ ሐምሌ ባለው ጊዜ የቤጂንግ ከሩሲያ የምትገዛው የነዳጅ ድፍድፍ፣ የነዳጅ ዘይት፣ የጋዝ እና የድንጋይ ከሰል ምርቶች ግዢ ከአመት በፊት ከነበረው 20 ቢሊየን ዶላር ወደ 35 ቢሊየን ዶላር አድጓል።

ለግዢው መጨመርም ከምዕራባውያን ማዕቀብ በኋላ ሩሲያ በሃይል አቅርቦት ምርቶቿ ላይ ያደረገችውን ቅናሽ ቻይና እንደመልካም አጋጣሚ መጠቀሟ ነው ተብሏል፡፡

ቻይና በሐምሌ ወር ብቻ ከሩሲያ 7 ነጥብ 4 ሚሊየን ቶን የድንጋይ ከሰል በማስገባት ከፍተኛውን ግዢ ስትፈጽም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ14 በመቶ ብልጫ አለው ነው የተባለው።

በሐምሌ ወር ከሩሲያ ወደ ቻይና የሚገባው የነዳጅ ድፍድፍ ከሰኔ ወር በትንሹ የቀነሰ ቢሆንም ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወር ጋር ሲነጻጸር አሁንም በ8 በመቶ ከፍ ያለ መሆኑ ተገልጿል።

ቻይና ከሩሲያ የተገበያየችው የተፈጥሮ ጋዝም ካለፈው ዓመት የ20 በመቶ ብልጫ ማሳየቱ ተጠቅሷል፡፡

ይህ አሃዝ ከሩሲያ ወደ ቻይና በዋናው የትራንስፖርት መስመር ቧንቧ የሚገባውን ነዳጅ እንደማያካትት ዘገባው አስታውሷል፡፡

በአጠቃላይ ቻይና በሐምሌ ወር ከሩሲያ ላስገባችው ነዳጅ 7 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር ወጪ እንዳደረገች የተገለጸ ሲሆን ባለፈው አመት በዚሁ ተመሳሳይ ወር ያወጣችው ወጪ 4 ነጥብ 7 ቢሊየን ዶላር እንደነበር አር ቲ በዘገባው አስታውሷል።