አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሽብር ቡድኑ ህወሓት ከመንግስት በኩል የቀረቡለትን በርካታ የሰላም አማራጮች ወደጎን በመተው ተኩስ መክፈቱን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ፡፡
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ዛሬ ባወጣው መግለጫ፥ መንግስት ተገዶ የገባበትን የሰሜኑን ጦርነት በሰላም ለመቋጨት ያስችላሉ ያላቸውን እርምጃዎች ሲወስድ መቆየቱን አስታውሷል።
በዚህም የሽብር ቡድኑ ህወሓት ከወረራቸው የአማራና የአፋር አብዛኞቹ አካባቢዎች ተገፍቶ እንዲወጣ ከተደረገ በኋላ መንግስት፥ ሙሉ የሰራዊትና ሎጂስቲክስ አቅም እያለው ወደ ትግራይ ክልል ከመግባት መቆጠቡ ጠቁሟል።
እንደዚሁም የተሳለጠና ያልተቋረጠ የሰብአዊ ድጋፍ ወደ ትግራይ ክልል እንዲገባ የተናጠል ተኩስ አቁም ማድረጉና ምቹ ሁኔታን መፍጠሩ፣ ለሰላም በር ይከፍታል በሚል እስረኞችን መፍታቱ እንዲሁም የሰላም አማራጭንም አሟጦ ለመጠቀም እንዲቻል የሰላም አማራጭ አብይ ኮሚቴን በይፋ ወደ ስራ አስገብቶ ግልጽ አቅጣጫንም ማስቀመጡን አስታውሷል።
አስፈላጊ የሆኑ መሰረታዊ ቁሳቁስ ወደ ትግራይ እንዲጓጓዝ ማድረጉን ያነሳው መግለጫው፥ ሆኖም አሸባሪው ቡድን ከውጪ ደጋፊዎቹ ጋር በመሆን ጦርነቱን የመቀጠል ከፍተኛ ፍላጎትን ሲያንጸባርቅ ቆይቷል ነው ያለው፡፡
በደቡብ ትግራይ በኩልም ተደጋገሚ ሙከራ ቢያደርጉም መንግስት ሙከራቸውን እያከሸፈ ዋናው መፍትሔ የሰላም መንገዱ ነው በሚል ጉዳዩ እንዳይባባስ ማድረጉ በመግለጫው ተነስቷል።
ሆኖም ከመንግስት በኩል የቀረቡለትን በርካታ የሰላም አማራጮች ሁሉ ወደጎን በመተው የሽብር ቡድኑ ህወሓት ታጣቂ ቡድን ሰሞኑን ሲፈጽም የሰነበተውን ትንኮሳ ገፍቶበት ዛሬ ንጋት ላይ በምስራቅ ግንባር በቢሶበር፣ በዞብል እና በተኩለሽ አቅጣጫዎች ከለሊቱ 11 ሰአት ጀምሮ ጥቃት ፈጽሟል።
በወሰደው እርምጃም ተኩስ ማቆሙን በይፋ አፍርሷል ያለው መግለጫው፥ የፈጸመው ጥቃትም ሆነ እሱን ተከትሎ ያወጣው መግለጫ አስቀድሞ ለትንኮሳው ሲዘጋጅ እንደነበር ግልጽ ማሳያ ነው ብሏል።
ጀግናው የኢፌዴሪ የመከላከያ ሰራዊትና መላው የጸጥታ ሃይል ከሽብር ቡድኑ የተሰነዘረውን ጥቃት በተቀናጀ መልኩ በድል እየመከቱት ይገኛሉም ነው መግለጫው።
በሃገር ውስጥም ሆነ በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ከዚህ የጥፋት ሃይል የሚሰነዘረውን ጥቃት ለመመከትና ኢትዮጵያን የመበተን ግልጽ አላማ የያዘውን ይህን የሽብር ቡድን የጥፋት ሙከራ ለማምከን በጋራ እንዲቆሙም መንግስት ጥሪውን አቅርቧል።
የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
የትግራይ ህዝብ ችግሮችን ለመፍታት ሰላማዊ አማራጭ ዛሬም፤ ነገም ብቸኛዉ መፍትሄ ነዉ!
መንግስት ተገዶ የገባበትን የሰሜኑን ጦርነት በሰላም ለመቋጨት ያስችላሉ ያላቸውን እርምጃዎች ሲወስድ መቆየቱ ይታወቃል። የሽብር ቡድኑ ህወሃት ከወረራቸው የአማራና የአፋር አብዛኞቹ አካባቢዎች ተገፍቶ እንዲወጣ ከተደረገ በኋላ መንግስት፤
• ሙሉ የሰራዊትና ሎጂስቲክስ አቅም እያለው ወደ ትግራይ ክልል ከመግባት መቆጠቡ