አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሚቀጥሉት አራት ዓመታት ውስጥ በፋይናንስ ዘርፍ 70 በመቶ ጎልማሶችን ለማካተት እየተሠራ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ገለጸ።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ፋይናንስ አካታችነት ጽሕፈት ቤት ዳይሬክተር ተመስገን ዘለቀ÷ በ2014 በጀት ዓመት በዘርፉ በተከናወኑ ተግባራትና የተገኙ ውጤቶችን በሚመለከት መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም÷ በኢትዮጵያ በፋይናንስ ስርዓቱ ውስጥ የተካተቱ ወይም የባንክ ሂሳብ ያላቸው ዜጎች ከ45 በመቶ እንደማይበልጡ ገልጸው÷ ይህም ከሰሀራ በታች ካሉ የአፍሪካ ሀገራት ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በሀገሪቱ 30 ሚሊየን ገደማ የሚጠጋው ጎልማሳ በፋይናንስ ተቋማት ምንም ዓይነት ሂሳብ እንደሌለው ጠቁመው÷ ለዚህም የፋይናንስ ተቋማት ቅርንጫፎች፣ ወኪሎች፣ ኤቲ ኤምን ጨምሮ ፖስ ማሽኖች በገጠሩ የሀገሪቷ ክፍል በሚፈለገው ደረጃ አለመሰራጨታቸው ምክንያት መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
የጥቃቅንና አነስተኛ የቁጠባና የብድር ሰጪ ተቋማትን ጨምሮ የኢንሹራንስ አገልግሎት ሰጪዎች ዝቅተኛ ገቢ ያለውን ማህበረሰብ ታሳቢ በማድረግ በኩል ውስንነት እንዳለባቸውም አብራርተዋል።
በተለይም በገጠሩ አካባቢ ያለው የፋይናንስ እውቀትና ክህሎት ዝቅተኛነት ሌላው ምክንያት መሆኑን ጠቁመው፥ መሰል ችግሮችን ለመፍታት ስትራቴጂ ጸድቆ ወደ ሥራ መገባቱን አብራርተዋል።
በ2014 በጀት ዓመት የሞባይል ገንዘብ ዝውውር 170 በመቶ እድገት ማሳየቱንና በሌላ በኩል በሰኔ 2013 ዓ.ም 92 ሚሊየን የነበረው የግብይት ሂሳብ ቁጥር እስከ ሰኔ 2014 ዓ.ም 131 ሚሊየን ከፍ ማለቱን አስረድተዋል።
ከዚህ ባለፈም በፋይናንስ ተቋማት ቅርንጫፎች፣ ወኪሎች እንዲሁም ፖስና ኤቴ ኤም ማሽኖች ተደራሽነት ላይ እድገት እንደታየ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡