አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ምርታማነታቸው በብሄራዊ ዝርያ አፅዳቂ ኮሚቴ የተረጋገጡ ስድስት አዳዲስ የሰብል ዝርያዎችን በምርምር ማውጣቱን አስታውቋል፡፡
የኢንስቲትዩቱ የሰብል ምርምር ዳይሬክተር ዶክተር አለማየሁ አሰፋ እንደገለጹት÷ በብሄራዊ ዝርያ አፅዳቂ ኮሚቴ ተገምግመው በ2014 በጀት ዓመት መጨረሻ የተለቀቁት የገብስ፣ የስንዴ፣ የዳጉሳ፣ የምግብ ሲናርና ሁለት የጤፍ ሰብል ዝርያዎች ናቸው፡፡
ከወጡት የሰብል ዝርያዎች መካከል አምስቱ ከአዴት ግብርና ምርምር ማዕከል መሆኑን ጠቅሰው የስንዴ ዝርያው ደግሞ ከደብረ ብርሃን ግብርና ምርምር ማዕከል የተገኘ ነው ብለዋል።
አዲሶቹ የሰብል ዝርያዎች ለተከታታይ ሶስት ዓመታት በተደረገ ምርምር÷ በሽታንና ድርቅን ተቋቁመው በሄክታር ከ21 ነጥብ 7 እስከ 49 ኩንታል ምርት መስጠት እንደሚችሉም አስረድተዋል።
ከደብረ ብርሃን ግብርና ምርምር ማዕከል የወጣው የስንዴ ዝርያ እስከ 49 ኩንታል ምርት መስጠት የሚችል መሆኑንም ነው የገለጹት።
ከአዴት ግብርና ምርምር ማዕከል የተገኘው የጥቁር ጤፍ ዝርያ በሄክታር እስከ 21 ነጥብ 7 ኩንታል ምርት መስጠት የሚችል መሆኑን ጠቅሰው፥ የጤፉ አይነት በደጋማ አካባቢዎች የበለጠ ውጤታማ እንደሆነ ተረጋግጧል ማታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
አዲስ የተለቀቀው የምግብ ገብስ ቀድሞ ፈጥኖ የሚደርስና በሄክታር 38 ነጥብ 4 ኩንታል ምርት መስጠት የሚችል በከፍተኛ ቦታዎች መመረት የሚችል መሆኑንም አመላክተዋል።
የዳጉሳ ዝርያው ደግሞ 32 ነጥብ 7፣ የምግብ ሲናሩ 45 ነጥብ 6 ኩንታል በሄክታር በአማካኝ ምርት መስጠት እንደሚችሉ አብራርተዋል።