አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 19 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የህወሓት ታጣቂዎች በዓለም ምግብ ፕሮግራም መጋዘን ውስጥ የፈጸሙት ዝርፍያ የትግራይን ህዝብ ለከፋ ረሃብ የሚዳርግ መሆኑን የዓለም ምግብ ፕሮግራም አስታወቀ።
አሸባሪው ህወሓት በመቀሌ በሚገኘው የዓለም ምግብ ፕሮግራም መጋዘን 12 ነዳጅ ቦቴ መዝረፉን ተመድ መግለጹ ይታወሳል።
የዓለም ምግብ ፕሮግራምም የህወሓት ታጣቂዎች የፈጸሙት ዝርፊያ አሳፋሪ መሆኑ ገልጿል።
አያይዞም ዝርፊያው በሰሜኑ ኢትዮጵያ በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎችን ለከፋ ረሀብ የሚዳርግ መሆኑንም ነው የገለጸው።
ላለፉት ጥቂት ወራት የነበረው የተኩስ አቁም የዓለም ምግብ ፕሮግራም እና አጋሮቹ በትግራይ ክልል ለሚገኙ ወደ 5 ሚሊየን ዜጎች የሰብአዊ እርዳታ እንዲያደርሱ አግዟቸው እንደነበርም አስታውሷል።
ይሁን እንጅ በትናንትናው እለት በቡድኑ የተፈጸመው ዝርፊያ ይህን ሰብአዊ ድጋፍ አደጋ ላይ እንደጣለው ነው ፕሮግራሙ ባወጣው መግለጫ ያስታወቀው።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ዴቪድ ቤስሊ የህወሓት ታጣቂዎች ትናንት ጠዋት መቀሌ በሚገኘው የዓለም ምግብ ፕሮግራም ቅጥር ግቢ ውስጥ ገብተው ከ500 ሺህ ሊትር በላይ ነዳጅ የተሞሉ 12 ቦቴዎች መዝረፋቸውን አስታውቀዋል፡፡
የተዘረፈው ነዳጅ በቅርቡ በድርጅቱ የተገዛና የዓለም ምግብ ፕሮግራም በትግራይ ክልል ለሚያደርገው ሰብአዊ ድጋፍን ጨምሮ፥ ምግብ፣ ማዳበሪያ፣ መድሃኒቶች እና ሌሎች የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፎችን ለማቅረብ የሚጠቅመበት መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም ያለነዳጅ በትግራይ ክልል ለዜጎች ለማድረስ እንደሚቸገርም አመላክተዋል፡፡
የነዳጁ መዘረፍ ለኃይል አቅርቦት እና ለመንቀሳቀስ የሚጠቀሙባቸውን ጀነሬተሮችን እና ተሽከርካሪዎችን እንዳይጠቀሙ ስለሚያደርጋቸው 5 ነጥብ 2 ሚሊየን ለሚሆኑና በችግር ላይ ለሚገኙ ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረስ አስቸጋሪ እንደሚያደርገውም አስረድተዋል።
በመሆኑም የሚመለከታቸው የትግራይ ባለሥልጣናት ሁኔታውን ከግምት ውስጥ አስገብተው በአስቸኳይ የዘረፉትን ነዳጅ እንዲመልሱ ጠይቀዋል፡፡
ድርጅቱ ዕርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች ድጋፉን ለማድረስ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፥ ይህን ተንቀሳቅሶ ለማድረግ ደግሞ ነዳጅ እንደሚያስፈልገው ልጸዋል፡፡
የተዘረፈው ነዳጅ እንዲሁም በሰሜን ኢትዮጵያ አቅርቦቱን ለማጓጓዝ በሁኔታዎች ያልተገደበ እንቅስቃሴ እንደሚያስፈልግ መግለጻቸውን የዓለም ምግብ ፕሮግራም መረጃ ያመላክታል።