የሀገር ውስጥ ዜና

አሸባሪው ህወሓት ወደ ትግራይ ክልል ሊያስገባ የነበረው አደገኛ ዕፅ ተያዘ

By Meseret Awoke

August 25, 2022

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው ህወሓት ወደ ትግራይ ክልል ሊያስገባ የነበረው አደገኛ ዕፅ መያዙን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አስታወቀ።

አሸባሪው የህወሓት ቡድን ከአዲስ አበባ እስከ ሚሌ ኔትወርክ በመዘርጋት በአፋር ክልል በኩል ወደ ትግራይ ክልል ሊያስገባው የነበረ በርካታ ኩንታል አደገኛ ዕፅ በህብረተሰቡ ጥቆማ እና በፖሊስ ብርቱ ክትትል ነው መያዙ የተጠቀሰው፡፡

ሁለት ተጠርጣሪዎች ቶዮታ ዶልፊን ተሽከርካሪ ላይ አደገኛ ዕፁን ጭነው ሲያጓጉዙ ህብረተሰቡ በሰጠው ጥቆማ መሰረት ከሌሎች የፀጥታና ደህንነት አካላት ጋር በመቀናጀት በቁጥጥር ስር ማዋሉን ፌደራል ፖሊስ አስታውቋል።

ከአደገኛ ዕፁ በተጨማሪ ለእኩይ ዓላማ ማስፈፀሚያ ሊውል የነበረ 2 ሚሊየን 370 ሺህ ብር መያዙንም ገልጿል።

በህወሓት የሽብር ቡድን አባልነት ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉት ሁለቱ ተጠርጣሪዎች በሚጠየቁበት ጊዜ አደገኛ ዕፁን የእርዳታ እህል የጫኑ ተሽከርካሪዎችን በመጠቀም ወደ ትግራይ ክልል ለማስገባት እንደሆነ ተናግረው ዕፁን ለመቀበል የተዘጋጀ ቡድን እንዳለም ጠቁመዋል።

ፖሊስም ይህንን ቡድን በቁጥጥር ስር ለማዋል በክትትል ላይ መሆኑን ነው ያስታወቀው።

ይህ የሽብር ቡድን ዕፁን ሊያስተላልፍ የነበረው እንደለመደው የትግራይ ወጣቶችን በዕፅ አደንዝዞ ወደ ጦርነት ለመማገድ እንደነበረ በቁጥጥር ስር የዋሉት ተጠርጣሪዎች መናገራቸውን ከፌዴራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

በየትኛውም ደረጃ የሚወጠኑ መሰል የወንጀል ተግባራትን ለመቆጣጠር ህብረተሰቡ ከፀጥታ አካላት ጋር ተገቢውን ቅንጅት በማድረግ የዜግነት ድርሻውን እንዲወጣ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጥሪውን አቅርቧል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!