አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሸባሪው ህወሓትን ዕድሜ ለማራዘም የትግራይ ሕዝብ የጦርነት ማገዶ መሆን እንደሌለበት ብልፅግና ፓርቲ ገለፀ።
የህወሓት አሸባሪ ቡድን በትግራይ ወጣቶች ደም ከመነገድ ባለፈ የሚፈይደው ነገር እንደማይኖር ከዚህ ቀደም በተግባር ታይቷል ያለው ፓርቲው፥ ቡድኑ ከዚህ በፊት ዕድሜያቸው ለውጊያ ያልደረሱ ልጆችን ጨምሮ ወጣቶችን ለጦርነት በመማገድ ያደረጋቸው ተከታታይ ጦርነቶች ሕዝብ ከማስጨረስ ውጪ ያስገኙለት ጥቅም የለም ብሏል፡፡
አሁንም አዲስ የተለየ ነገር እንደማይፈጥሩለት ሊገነዘብ ይገባል ብሏል ፓርቲው፡፡
የሕዝብ ጥያቄ የሚመለሰው ልማትንና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታን በማጠናከር እንጂ ሁልጊዜ የጦርነት ነጋሪት በመጎሰም አለመሆኑንም በአጽንኦት ገልጿል ፓርቲው፡፡
የህወሓት መሪዎች ኢትዮጵያን የማተራመስና የመበታተን ምኞታቸው መቼም እውን እንደማይሆን በመረዳት የጥፋት እጃቸውን እንዲሰበስቡ አሳስቧል፡፡
አሸባሪው ቡድን ከምስረታው ጀምሮ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ለማጥፋት የቀየሰው የጥፋት ስትራቴጂ እንደማያዋጣው ተገንዝቦ የሰላሙን ጥሪ እንዲቀበል በማድረግ ረገድ የትግራይ ሕዝብ ከፍተኛ ኃላፊነት አለበት ብሏል ፓርቲው፡፡
ይህ የጥፋት ኃይል ወደ ሰላም ድርድር እንዲመለስ በተለያዩ አማራጮች ጫና ማሳደር እንደሚገባም ነው የጠቆመው።
የትግራይ ሕዝብ የአሸባሪውን ቡድን ዕድሜ ለማራዘም ሲባል ብቻ ወደ ጦርነት ሲማገድ መቆየቱን የገለጸው ፓርቲው፥ ይህም መቀጠል የለበትም ብሏል፡፡
የትግራይ ሕዝብ የህወሓት ቡድን እያደረሰበት ያለው ስቃይ የሚያበቃበትን መስመር እንዲከተል ማስገደድ እንደሚጠበቅበትም አመላክቷል፡፡