አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 7 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በሃገራችን የተከሰተውን የኮሮና ቫይረስ መከላከል ይቻል ዘንድ ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አሳሰበ።
በኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በኩል የተሳተፉ የተለያዩ የሃይማኖት መሪዎች በሃገሪቱ የተከሰተውን የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል ህብረተሰቡ የግል እና የአካባቢ ንጽህና ላይ እንዲያተኩርና ከተለመደው የአኗኗር እና የሰላምታ አሰጣጥ ዘይቤ በመውጣት ጥንቃቄ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።
የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከልም ሁሉም አካላት ሃላፊነታቸውን እንዲወጡም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ፈጣሪን ከሚያስቆጣ ተግባራት ከመቆጠብ ጀምሮ በሽታውን ለመከላከል ይጠቅማሉ ተብሎ የተቀመጡ ምክረ ሃሳቦችን ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋልም ብለዋል።
የግል እና የአካባቢ ንፅህናን መጠበቅ፣ ህዝብ ከሚሰበሰብባቸው አካባቢዎች ራስን መግታት፣ በሃይማኖት ተቋማት ውስጥም ቢሆን ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋልም ነው ያሉት።
አጠራጣሪ ነገሮች ሲከሰቱም ወደ ህክምና ተቋማት መሄድ እና መጠቆም የሁሉም ዜጎች ተግባር መሆን እንዳለበትም አንስተዋል።
የነጋዴው ማህበረሰብ በዕቃዎች ላይ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ ማድረግ ከሰብዓዊነት አንጻር የማይደፈር እንዲሁም በመንፈሳዊውም ሀጥያት ነውና ከዚህ ተግባር እንዲቆጠቡም አሳስበዋል።
የሃይማኖት መሪዎቹ ቀደም ብለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ ጎበኝተዋል።
በተስፋዬ ከበደ እና ማርታ ጌታቸው
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ! https://t.me/fanatelevision