የሀገር ውስጥ ዜና

የአሸባሪው ህወሓት የአፍሪካ ኅብረትን የሠላም ጥረት ከማንኳሰስ ድርጊት ጀርባ – በፒፕልስ ዲስፓች ዘገባ ሲጋለጥ

By Alemayehu Geremew

August 31, 2022

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው የህወሓት ቡድን ሦስተኛ ዙር ጦርነት ከመጀመሩ ከቀናት በፊት የአፍሪካ ኅብረትን የሰላም ጥረት ማንኳሰስ ጀምሮ ነበር፡፡

አሸባሪው የህወሓት ቡድን አፈቀላጤዎች በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ላይ በሚበትኗቸው ፅሁፎች “ቀድሞውንም ቢሆን በኢትዮጵያ መንግስት እቅፍ ውስጥ ባለው በአፍሪካ ኅብረት የተመራ የሠላም ድርድር መቀበል ስህተት ነበር” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

ቡድኑ ድርድሩን ምዕራባውያን እንዲቀበሉት በፈረንጆቹ ነሐሴ 22 ቀን በአፍሪካን ሪፖርት ላይ በጻፈው ሃሳብ ጠይቋል፡፡

ፒፕልስ ዲስፓች አንድ የታሪክ ምሁርን ዋቢ አድርጎ በጽሑፉ እንዳመላከተው ህወሓት የምዕራባውያኑን ጣልቃ ገብነት መጠየቁ ቀድሞውኑም ቢሆን የውጭ ሀይሎች ጉዳይ አስፈፃሚ እና አጀንዳቸውን በኢትዮጵያ ላይ ሊፈፅሙ የሚጋልቡት መሆኑን በግልፅ ያጋለጠ ነው ብሏል፡፡

አሸባሪ ቡድኑ ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄን ከሚሻው የአፍሪካ ህብረት ይልቅ ምዕራባውያን የሰላም ሂደቱን እንዲመሩ መጠየቁ በተለይም የአሜሪካና አውሮፓ ሀገራት ጉዳይ አስፈፃሚነቱን የሚያሳይ ነው ሲል ጽሑፉ ያነሳል፡፡

ህወሓት በአሜሪካ ድጋፍ ከፈረንጆቹ 1991 ጀምሮ ኢትዮጵያን በአምባገነንነት ሲመራ ጥያቄ የሚያነሳ አካል እንዳልነበርም ዘገባው አስታውሷል፡፡

ከአሸባሪ ቡድኑ ጀርባ አሜሪካ ስላለች ከገዢ ፓርቲ ውጪ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገሪቷ ጉዳይ ላይ የመወሰን ዕድል እንዳይኖራቸው ታግደው መቆየታቸውንም ፒፕልስ ዲስፓች ይጠቁማል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላም ከኤርትራ እና ሶማሊያ ጋር ያሉ ግጭቶችን በሠላማዊ መንገድ ለመፍታት የተደረሰው የሦስትዮሽ ስምምነት በአሜሪካ እና በአውሮፓ ኅብረት በበጎነት እንዳልታየ ነው የተገለጸው፡፡

ምክንያቱም ስምምነቱን ተከትሎ በጊዜ ሂደት አሜሪካ በአፍሪካ ጉዳይ ላይ የሚኖራት የበላይነት እና ጣልቃ ገብነት እንደሚቀንስ በመሰላቱ መሆኑም ተመላክቷል፡፡

ለአብነትም ሲል በአፍሪካ ቀንድ ላይ የሚፈጠሩ ህብረቶች አፍሪኮምን የመሰሉ የአሜሪካ ወታደራዊ ፕሮጀክቶችን ሚና አልባ እስከማድረግ የሚደርስ ተፅእኖ ሊኖራቸው እንደሚችል አሜሪካ በመፍራቷ መሆኑንም ይዘረዝራል።

ፅሁፉ ህወሓት አሜሪካ በድጋሚ ጣልቃ የምትገባበትን ዕድል ማመቻቸት የፈለገው አሜሪካ በቀጣናው ያጣችውን ተሰሚነት ለመመለስና ለውለታው ምላሽ ተጠቃሚ የሚሆንበትን መንገድ ለማግኘት መሆኑም የተለያዩ ምሁራንን በማናገር በፃፈው ሀተታ አመላክቷል፡፡