የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያ ስጋ ደዌ ተጠቂዎች ብሄራዊ ማህበር የስልጠና ማዕከል አስመረቀ

By Amele Demsew

September 02, 2022

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ስጋ ደዌ ተጠቂዎች ብሄራዊ ማህበር ለገቢ ማስገኛና ለስልጠና አገልግሎት የሚውል ማዕከል አሰርቶ አስመረቀ፡፡

ማህበሩ ለአባላቱ ገቢ ማስገኛና ለስልጠና አገልግሎቶች የሚውል 1 ሺህ 500 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ ባለአምስት ወለል ህንጻ ነው አሰርቶ ያስመረቀው፡፡

በምረቃ መረሐ ግብሩ የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ፣ የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰን ጭምሮ ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች እና ጥሪ የተደረገላቸው ተገኝተዋል፡፡

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ ማዕከሉ በዋናነት አቅመ ደካማ የሆኑ የሥጋ ደዌ ተጠቂ አካል ጉዳተኞች፣ ወላጅ ያጡ ህጻናትን፣ አረጋውያንና ሴቶችን እንዲሁም ተፈናቃዮች እንደሚደጎሙበት ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

የስልጠና ማዕከሉ አካል ጉዳተኞች ዘንድ የይቻላልን መንፈስ ለማስረጽ እና የኢኮኖሚያዊ ችግሮቻቸውን ቀርፈው ከጥገኘነት እንዲላቀቁ እንደሚያግዝም ተገልጿል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት በኢትዮጵያ ተወካይ ቦሪይማ ሃማ በበኩላቸው ÷በሳሳካዋ አጋዥነት ለተሰራው ማዕከል አድናቆታቸውን ገልጸው ድርጅታቸው በቀጣይ በስጋ ደዌ ምክንያት የሚከሰቱ የጤና እክሎችን ለመቅረፍ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡

የሳሳካዋ ግሎባል ፋውንዴሽን መስራች ዮሂ ሳሳካዋ ለማህበሩ የሚያደርገውን ድጋፍ እንደሚያጠናክር እንዲሁም በትብብር የመስራት ሂደቱንም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ታካኮ ኢቶ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ዘርፈ ብዙ ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መግለጻቸውን ከሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡