የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያና ቱርክ በስራ እድል ፈጠራና ቴክኖሎጂ ሽግግር ያላቸው ትብብር ከፍተኛ ነው ተባለ

By Meseret Awoke

September 02, 2022

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያና ቱርክ በስራ እድል ፈጠራና ቴክኖሎጂ ሽግግር ያላቸው ትብብር ከፍተኛ መሆኑን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሳንዶካን ደበበ ገለጹ፡፡

ዋና ስራ አስፈጻሚው በኢትዮጵያ የቱርክ አምባሳደር ያፕራክ አልፕ ጋር በድሬዳዋ የንግድ ቀጠናና በኢንዱስትሪ ፓርኮች ስለሚገኙ የኢንቨስትመንት አማራጮችና የቴክኖሎጅ ሽግግር ላይ ተወያይተዋል፡፡

አቶ ሳንዶካን የቱርክ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በሚገኙ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሥራ እድል በመፍጠርና የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማቀላጠፍ በኩል እየሰሩት ያለው ስራ ከፍተኛ መሆኑን ለአምባሳደሯ አብራርተውላቸዋል፡፡

ቱርክ በነጻ የንግድ ቀጠና ዘርፍ ልምድ ካላቸው ሀገራት መካከል ግንባር ቀደም መሆኗን የገለጹት አቶ ሳንዶካን ፥ የቱርክን ልምድ በኢትዮጵያ በማስፋት በዘርፉ የተሻለ ስራን ከመስራት በተጨማሪም ባለሃብቶች በዘርፉ መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ የሚያስችሉ አማራጮች በመከናወን ላይ ናቸው ብለዋል።

በኢትዮጵያ የቱርክ አምባሳደር ያፕራክ አልፕ በበኩላቸው እንዳሉት ፥ ቱርክና ኢትዮጵያ በባህል፣ በታሪክ፣ በፖለቲካ የጠነከረ ትስስር አላቸው፡፡

አክለውም ግንኙነቱን አጠናክሮ ለማስቀጠል ትኩረት ሰጥተው በመስራት ላይ እንደሚገኙ መናገራቸውን ከኮርፖሬሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

የሁለቱን ሃገራት ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ሀገራቸው በነጻ የንግድ ቀጠናና በኢንዱስትሪ ፓርኮች ላይ ያላትን ልምድ በማካፈል ኢትዮጵያ በዘርፉ ውጤት እንድታስመዘግብ እንደሚደግፉም ነው የተናገሩት።

አምባሳደሯ አክለውም ፥ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች በርካታ መሆኑ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በዘርፉ እንዲሰማሩ የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡም ገልጸዋል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!