የሀገር ውስጥ ዜና

የባንክ ዘርፍ ለውጭ ባለሃብቶች መከፈት በባንክ ዘርፍ ውስጥ ትልቅ ለውጥ እንደሚያመጣ ተገለፀ

By Meseret Awoke

September 04, 2022

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 29፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የባንክ ዘርፍ ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት መደረጉ በኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ ውስጥ ትልቅ ለውጥ የሚያመጣ እንደሆነ ተገለፀ።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባካሄደው 13ኛ መደበኛ ስብሰባ የባንክ ዘርፍን ለውጭ ኢንቨስተሮች ክፍት ለማድረግ በቀረበ ፖሊሲ ላይ ተወያይቶ በሥራ ላይ እንዲውል መወሰኑ ይታወቃል።

ይህን ተከትሎ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፥ ኢትዮጵያን ለኢንቨስትመንት ተወዳዳሪና ተመራጭ የሚያደርግ መሰረታዊ ለውጥ የሚያመጣ ውሳኔ መሆኑን ነው የገለጹት።

በተጨማሪም የፋይናንስ ኢንደስትሪውን በማዘመን ኢኮኖሚውን ለማሳደግ የማይተካ ሚናውን ይጫወታል ብለዋል::

የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ ውሳኔውን ታሪካዊ ነው ብለውታል፡፡

ባለሙያው አክለውም፥ ከ50 ዓመታት በኋላ የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ ያፀደቀው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ ትልቅ ለውጥ ይዞ ብቅ እንደሚል ያላቸውን እምነት ነው የጠቀሱት፡፡

ፖሊሲው ወደ ስራ ሲገባ የኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ ትልቅ ለውጥ እንደሚያመጣ ይጠበቃልም ብለዋል፡፡

የባንክ ዘርፍን ለውጭ ኢንቨስተሮች ክፍት ማድረግ የዘርፉን አገልግሎቶች በእውቀት እና በቴክኖሎጂ ለመደገፍ፣ የአገራችን ኢኮኖሚ ከዓለም አቀፍ ገበያ ጋር ያለውን ትስስር ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር፣ የፋይናንስ ዘርፉን ተወዳዳሪነት፣ ውጤታማነትና ቀልጣፋነት በመጨመር በቂ የፋይናንስ አቅርቦት እንዲኖር የሚያስችል ፖሊሲ ነው የጸደቀው፡፡

ፖሊሲው የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት እንዲሳለጥ፣ የሚፈጠረው የሥራ ዕድል እንዲጎለብት፣ ኢኮኖሚያዊ ውጤታማነትን እና ዓለምአቀፍ ተወዳዳሪትን በማረጋገጥ ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት ለማረጋገጥ የሚያስችል መሆኑም ተመልክቷል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!