አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 29፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ እና አፋር ክልሎች አሸባሪው የህወሓት ቡድን ያደረሰውን አስከፊ ሰብዓዊ ቀውስ ኒውዝላንዳዊው ጋዜጠኛ አልስተር ቶምሰን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡
አልስተር ቶምሰን ከጋዜጠኝነት በተጨማሪ በሕዝብ ግንኙነት ባለሙያነት እና በጂኦፖለቲካ ተንታኝነታቸው ይታወቃሉ፡፡
አልስተር ቶምሰን በዚህ ዓመት ሚያዝያ ወር ላይ ወደ ኢትዮጵያ እንደመጡና እስከ ሰኔ መቆየታቸውንም ከጣቢያችን ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ለሁለት ወራት በነበራቸው ቆይታም ጎንደርን ጨምሮ በሌሎች የአማራ ክልል አካባቢዎች እና በአፋር በጦርነት የተጎዱ ቦታዎችን መጎብኘታቸውን ጠቁመዋል።
ጋዜጠኛው በድንበር ለትግራይ ቅርብ በሆኑት ወልቃይት እና አብ ዓላ አካባቢዎች ሄደው አስከፊ የሰብዓዊ ቀውስ መመልከታቸውንም ነው የተናገሩት፡፡
በወቅቱ አብ ዓላ በሚባለው አካባቢ መኪና በሚያሽከረክሩበት ወቅት ወደ ትግራይ የሚጓዙ 108 የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት የጫኑ መኪኖችን መመልከታቸውንም አስታውሰዋል፡፡
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ወደ ትግራይ የሚጓዙት የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት ጭነት መኪናዎቹ ቁጥር እያደገ እንደመጣና ወደ 300 እንደደረሰ መረጃ እንዳላቸውም አውስተዋል፡፡
ጋዜጠኛ አልስተር ቶምሰን ÷ በአፋር ዱብቲ የሚገኝ ኢ-መደበኛ በሆነ መልኩ ተፈናቃዮች የሠፈሩበትን መጠለያ ጣቢያ መጎብኘታቸውን አንስተዋል።
መጠለያ ጣቢያው ለተፈናቃዮች ኑሮ እጅግ ፈታኝ እንደነበረና የውሃ አቅርቦት ዕጥረት እንደነበረበትም ነው ጋዜጠኛው የጠቆሙት፡፡
የመጠለያ ጣቢያው ነዋሪዎች በቤተሰብ በቀን 25 ሊትር ያህል ውሃ ብቻ ሲያገኙ እንደነበረና ይህም ቦታው ሞቃት ከመሆኑ ጋር ተዳምሮ ኑሯቸውን ፈታኝ እንዳደረገባቸውም ነው የሚናገሩት።
በወቅቱ በዱብቲ ሆስፒታል የሚሰሩ ሐኪሞችም በአካባቢው የአጣዳፊ ተቅማጥ ወረርሽኝ ይከሠታል የሚል ሥጋት እንደነበረባቸውም ጠቅሰዋል።
በየቀኑ 2 እና 3 ሕፃናት ሕይወታቸው ሲቀጠፍ እንደነበረና በአጠቃላይ በቁጥር በርካታ የሆኑ ሕጻናት አካባቢው ላይ ሕይወታቸውን እንዳጡም አስታውሰዋል፡፡
አሸባሪው የህወሓት ቡድን በአፋርና አማራ ክልሎች በፈጸመው ወረራ በርካታ ዜጎች ከአካባቢያቸው መፈናቀላቸውን እና ለኑሮ አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ላይ ይገኙ እንደነበርም ጋዜጠኛው አብራርተዋል፡፡
አሁንም ህወሓት ተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ እንደተዘፈቀና መንግስት በተደጋጋሚ ያቀረበለትን የሰላም አማራጭ አሻፈረኝ ብሎ እንደገና ወደ ጦርነት እንደገባ ጠቁመዋል፡፡
በቆቦ እና አካባቢው በርካታ ንፁሃን ዜጎችን መግደሉንም ነው የገለጹት።
ነገር ግን አይኑን በጨው ታጥቦ እንደተበደለ እና ወረራ እንደተፈፀመበት እያስመሠለ ነውም ብለዋል፡፡