አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲሱ ዓመት አቀባበል ፈተናዎችን በድል ለመወጣት የሚያስችል መደላድል በሚፈጥር መልኩ እንደሚከበር የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለጹ፡፡
አቶ ኦርዲን መጪውን አዲስ አመት አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት÷ በአመቱ የታዩ ስኬቶችንና የገጠሙ ፈተናዎችን መነሻ በማድረግ አምስቱን የጳጉሜን ቀናት ” ጳጉሜን በመደመር” በሚል መሪ ሐሳብ በተለያየ መርሐ ግብር ይከበራሉ፡፡
በዚሁ መሠረት÷ ጳጉሜን 1 የበጎ ፈቃድ ቀን፣ ጳጉሜን 2 የአምራችነት ቀን፣ ጳጉሜን 3 የሰላም ቀን፣ ጳጉሜን 4 የአገልጋይነት ቀን እንዲሁም ጳጉሜን 5 የአንድነት ቀን በሚል ስያሜ በክልል ደረጃ ይከበራል፡፡
መርሐ ግብሮቹ የተሳኩ እንዲሆኑ ሁሉም የመንግስት ተቋማት፣ በየደረጃ የሚገኝ አመራር፣ የመንግስት ሠራተኞችና መላው ሕዝብ የሚጠበቅበትን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
አዲሱን አመት ስንቀበል ለስኬት ያበቁንን ተሞክሮዎች በማጉላት ለተጨማሪ ድሎች እንዲሁም የተጋረጡ ፈተናዎችን በድል ለመወጣት የሚያስችሉ መደላድሎችን በሚፈጥር መልኩ ነው ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመለክታል፡፡