የሀገር ውስጥ ዜና

በአሜሪካ፣ አውሮፓና አፍሪካ የሚኖሩ ዳያስፖራዎች በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ተወያዩ

By Alemayehu Geremew

September 05, 2022

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሜሪካ፣ አውሮፓና አፍሪካ የሚኖሩ ዳያስፖራዎች በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ ተወያይተዋል፡፡

ዳያስፖራው የኢትዮጵያን ጥቅም በሚያስጠብቁ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ተሳትፎና ውግንና እንዲያጠናክሩ ጥሪ ቀርቦላቸዋል።

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ስለሺ በቀለ በአሜሪካ ከሚገኙ የፐብሊክ ዲፕሎማሲና አድቮኬሲ ተቋማት መሪዎች ጋር በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ በበይነ መረብ ውይይት አድርገዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት አሁንም ለሰላም የማያወላውል አቋም እንዳለው አስረድተዋል።

ዳያስፖራው የሽብር ቡድኑ ሐሰተኛ ፕሮፓጋንዳና ወረራ ከማጋለጥ አንጻር እያከናወናቸው ያላቸውን ስራዎች አስመልክቶ ግምገማ መደረጉንም በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።

በተጨማሪ በፈረንሳይ፣ ስፔን፣ፖርቹጋል እና ሞናኮ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሄኖክ ተፈራ ÷ በሀገራቱ ከሚገኙ ዳያስፖራዎች ጋር ጦርነቱን በተመለከተ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተደረገውን ጥረት በበይነ መረብ በተካሄደው ውይይት አስረድተዋል፡፡

ሕወሓት ግን አሻፈረኝ ብሎ ጦርነት እንደከፈተ አምባሳደሩ ማስረዳታቸውን ከኢዜአ ያገኘኘው መረጃ ያመላክታል።

በተመሳሳይ በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሙክታር ከድር በክዋዙ ናታል ግዛት ፒተር ማርትስበርግ ከተማ ከሚገኙ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማኅበረሰብ አባላት ጋር በወቅታዊ ሁኔታ ላይ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

ዳያስፖራዎቹ በአንድነት በመቆም ኢትዮጵያን የገጠሟትን ፈተናዎች እንድትሻገር አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያድጉ መግለጻቸውን አመላክተዋል።