የሀገር ውስጥ ዜና

በክልሎች የበጎፈቃድ ቀን እየተከበረ ነው

By Meseret Awoke

September 06, 2022

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በክልሎች “ጳጉሜን በመደመር” በሚል ሐሳብ የበጎ ፈቃድ ቀን በበጎ ተግባራት እየተከበረ ነው።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እየተከበረ በሚገኘው የበጎፈቃድ ቀን ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰንና ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

ዕለቱን ምክንያት በማድረግ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ ተማሪዎች የትምህርት መማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ ተደርጓል።

ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ የትምህርት ቁሳቁሱን ሲያስረክቡ እንደገለጹት ፥ ብዝሃነት ባለበት ሀገር በጎ ማሠብና መሥራት አስፈላጊና ጠቃሚ ነው፡፡

በተመሳሳይ በጋምቤላ ክልል ቀኑ ለወባ መራቢያ የሆኑ ቦታዎችን በማጽዳትና ደም በመለገስ እየተከበረ ሲሆን ፥ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ እና ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ታንኳይ ጆክና ሌሎች የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

አቶ ኡሞድ ኡጁሉ እንዳሉት፥ የ2015 ዓመትን ስንቀበል ለስኬት ያበቁንን ተሞክሮዎችና እሴቶቻችንን በማጉላት፣ የተጋረጡብንን ፈተናዎች በድል በመወጣት ሊሆን ይገባል።

በተጨማሪም ዕለቱን አስመልክቶ የደም ልገሳ መርሐ ግብር በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ተካሂዷል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሃር፣ የአስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮችና፣ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ደም ለግሰዋል፡፡

ከንቲባ ከድር ጁሃር በበጎ ፍቃድ ደም ልገሳ መርሐ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ፥ በጎ ፍቃድ ቀንም ይሁን በሌሎች ቀናት ደማችንን ለወገናችን በመለገስ ህይወት የማዳን በጎ ተግባር ልንፈፅም ይገባል ብለዋል፡፡

በሐረሪ ክልል ቀኑ ታስቦ ሲውል ለአቅመ ደካማ ወገኖች የታደሱ ቤቶች የተመረቁ ሲሆን፥ ለአረጋውያንና አቅመ ደካማ ወገኖች የምግብና የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ድጋፍ እንዲሁም የደም ልገሳ መርሐ ግብር ተካሂዷል።

መርሃግብሩን ያስጀመሩት የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ፥ አንድነታችንን ማጠናከርና በሀገር ላይ የተደቀነውን አደጋ መመከት እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።

የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የእለት ተእለት ተግባር ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመው ፤ በመርሐ ግብሩም ሀይማኖት፣ ዘርና ፆታን ሳንለይ ሁሉንም በበጎነት ስሜት ማገልገል እንደሚገባ ገልጸዋል።

ምንጭ ፡ – የክልሎቹ ኮሙኒኬሽን ጽሕፈት ቤት

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!