አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በልደታ ክፍለ ከተማ በሁለት ወራት የተገነቡ ሦስት ባለ 11 ወለል ዘመናዊ ሕንጻዎችን መረቁ፡፡
ከንቲባ አዳነች በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ “ጳጉሜን በመደመር ስንል ምክንያታችን ትልቅ ነበር፤ በሰው ተኮር ዕቅዳችን መነሻነት በዘጠና ቀናት 952 ቤቶችን በጎ ፈቃደኞችን በማስተባበር ገንብተን በሁሉም ክፍለ ከተሞች ቁልፍ አስረክበናል” ብለዋል፡፡
በሚቀጥለው አዲስ ዓመትም በ24-ሰባት መርህ በርካታ ሥራዎችን ለመሥራት ዘርፈ ብዙ ቅንጅታዊ እንቅስቃሴ እያደረግን ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች÷ በርካታ ስኬቶችን በቅንጅት፣ በአንድነትና በወንድማማችነት እንደሚያስመዘግቡ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
በትብብር መንፈስ ሁሉም የድርሻቸውን ማህበራዊ ኃላፊነት መወጣት ቢችል÷ የአቅመ ደካማ ወገኖች የኑሮ ጫና በሚፈለገው ደረጃ ማቃለል ይቻላልም ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች፡፡
የሀገር መከላከያ ሰራዊትና የጥምር ጦሩ ለሀገር እየተዋደቁ እና የልማት ሥራዎችን እየከወንን ስለሆነ ካለን ላይ ቀንሰን አስፈላጊውን ድጋፍ ልናደርግላቸው ይገባል ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
መጪው ዘመን ኢትዮጵያ የምታሸንፍበት ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች÷ በፍጹም ላንነጣጠል በአንድነትና በወንድማማችነት መንፈስ በሁሉም ረገድ ኢትዮጵያ የሚፈጸምባትን ጥቃት ልንከላከልና ጸንተን ልንመክት ይገባልም ብለዋል ባስተላለፉት መልዕክት፡፡
በዛሬው ዕለት በልደታ ክፍለ ከተማ 150 ቤቶችን የያዘ ሦስት ባለ 11 ወለል ሕንጻ ተገንብቶ ለ165 አባዎራዎች መተላለፉን የከንቲብ ጽሕፈት ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡