አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሸባሪው ህወሓት ቡድን ከሌሎች አሸባሪ ቡድኖች ጋር ኅብረት ፈጥሮ እየሠራ ስለመሆኑ በቅርቡ አፈትልኮ የወጣው ምስጢራዊ ሰነዱ ያመለክታል።
ቡድኑ ያዘጋጀው “የማጠቃለያ ምዕራፍ አካሄድና ስትራቴጂ” በሚል ያዘጋጀው እና ሾልኮ የወጣው ሰነዱ፥ በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሰው የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት የትግል አጋሩ መሆኑን ይጠቅሳል።
አሸባሪው ሸኔ መንግሥት በወሰደው እርምጃ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበትም ሰነዱ አጋላጧል፡፡
በመሆኑም የፌደራል መንግሥት በሸኔ ላይ በወሰደው እርምጃ ከፍኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው ሰነዱ “ግንባር ላይ የሚገኙ የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት አመራሮች እንደሚነግሩን ከፍተኛ ጉዳት እየደረሳቸው እንዳለና የትግል ስልት መቀየር ግዴታ እንደሆነባቸው ማየት ተችሏል” ሲል አትቷል፡፡
ከኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት አመራር ጃል ሚልኬሳ ጋር በምስጢር ባደረግነው ውይይት÷ በአጭር ጊዜ አመራራቸው ወደሚመች አካባቢ (ወደ አጎራባች ሀገራት) ስልታዊ ማፈግፈግ የሚያደርጉበት ሁኔታ እንዲመቻች እና የመከላከል አቅምና ዝግጁነት የሌላቸው የሠራዊቱ አባላት ከተቻለ ዩኒፎርማቸውን ጥለው ወደ ሕዝቡ እንዲቀላቀሉና እንዲደበቁ ካልተቻለም ለመንግሥት ኃይሎች እጃቸውን መስጠት የተሻለ አማራጭ እንደሆነ አንስቶ ነበር ብሏል ሰነዱ፡፡
እዚህ ላይ በግልጽ እንደምንረዳው ህወሓት ከአሸባሪው ሸኔ ጋር ቁርኝት በመፍጠር ቡድኑን በጥልቀት አውቆ በትብብር እየሠራ ስለመሆኑ ነው።
“የፌደራል እና የኦሮሚያ ክልልን አካሄድ ሽባ በማድረግ ወደ አዲስ አበባ ለሚደረገው የመጨረሻ የትግል ምዕራፍ የቅርብ አጋዦች የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት በመሆናቸው” ሲል ቡድኑን ልክ እንደከዚህ ቀደሙ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)ን ወደ አዲስ አበባ ለመግባት እና ስልጣን ላይ ለመውጣት እንደተጠቀመው ከዚያም አሽቀንጥሮ እንደጣለው አሁንም ሸኔን ለተመሳሳይ ተልዕኮ እንደሚጠቀም በግልፅ አስፍሯል።
የህወሓትን ከሌሎች የሽብር ቡድኖች ጋር ያለውን ጋብቻ የሚያሳየው ሌላኛው የሰነዱ ክፍል ስለ አልሸባብ የሚጠቅሰው ነው።
“በሶማሌ ክልል ከሚንቀሳቀሱ እና የጋራ ጠላታችን የሆነውን መንግሥትን ከሚታገሉ የአልሸባብ ሴሎችና ከኦጋዴን ታጋዮች ጋር የመረጃ ልውውጥ እገዛ እና ስትራቴጂ ሥራዎቻችን ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል “ ሲል አብረው እንደሚሠሩ አጋልጧል።
በቅርቡ አፈትልኮ የወጣው ምስጢራዊው የአሸባሪው ህወሓት ሰነድ እንደሚያረጋግጠው÷ የህወሓት ቡድን ህወሓት ሀገር ለማፍረስ ከሌሎች አሸባሪ ቡድኖች ጋር ኅብረት ፈጥሮ እየሠራ መሆኑን ነው፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!