የሀገር ውስጥ ዜና

በአማራ ክልል የባለሀብቶች ወቅታዊ ኮሚቴ እና ደብረ ብርሃን ከተማ ለጥምር ጦሩ ድጋፍ አደረጉ

By Shambel Mihret

September 06, 2022

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል የባለሀብቶች ወቅታዊ ኮሚቴ እና የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር በግንባር ለሚገኘው ጥምር ጦር ከ5 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያለው የዓይነትና የሰንጋ ድጋፍ አደረጉ።

የአማራ ክልል ባለሀብቶች ወቅታዊ ኮሚቴ÷ በሰሜን ጎንደር ዞን በሰሜን ማይጠብሪ ተከዜ ግንባር የአሸባሪውን ህወሓት ወረራ እየመከተ ለሚገኘው ጥምር ጦር 100 የእርድ ሰንጋዎችን ድጋፍ አድርጓል።

የአማራ ባለሀብቶች ወቅታዊ ኮሚቴ የሎጅስቲክ አስተባባሪ ሙሉጌታ ቢያዝን እንደገለጹት÷ ባለሃብቶቹ 3 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ግምት ያላቸው ሰንጋዎችን ድጋፍ አድርገዋል፡፡

በቀጣይም ድጋፋችንን እንቀጥላለን ማለታቸውን የሰሜን ጎንደር ዞን ኮሙኒኬሽን መረጃ አመላክቷል፡፡

በተመሳሳይ የደብረብርሃን ከተማ ነዋሪዎች ለጥምር ጦሩ ድጋፍ አድርገዋል፡፡

የከተማዋ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት እንደገለጹት÷ የሕዝብ ጠላት የሆነውን ቡድን ለመደምሰስ በሚደረገው ርብርብ የከተማዋ ሕዝብ የደጀንነት ተግባሩን የስንቅ ድጋፍ በማድረግ አሳይቷል ብለዋል፡፡

ድጋፉም የእርድ ሰንጋን ጨምሮ ምግብ ነክ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሶችን ያካተተ ግምቱም÷ 2 ሚሊየን 243 ሺህ 600 ብር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሰላማዊት ሙሉነህ