አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከ123 ሺህ በላይ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች ማዕድ ማጋራቱን አስታወቀ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በሚሊኒየም ኣዳራሽ ማዕድ ሲያጋሩ ባደረጉት ንግግር፥ በመዲናዋ ከ123 ሺህ ለሚበልጡ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች 365 ሚሊየን 658 ሺህ ብር በላይ ወጪ በማድረግ ማዕድ አጋርተናል ብለዋል፡፡
ለወገኖቻችን የምናጋራው ቁስ ብቻ ሳይሆን÷ ልባዊ ፍቅራችንን፣ መተሳሰባችንን፣ አብሮነታችንን እና አንዳችን ለአንዳችን ድጋፍና ምርኩዝ መሆናችንን ጭምር ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የበጎ ፈቃደኝነትን ቀን ምክንያት በማድረግ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች ያለንን ፍቅር፣ አብሮነትና ዘላቂ አጋርነት በተግባር ለማረጋገጥ በ11ክፍለ ከተሞች ማዕድ አጋርተናል ብለዋል፡፡
አስተዳደሩ የአቅመ ደካማ ወገኖችን ኑሮ የሚያቃልሉ ሥራዎችን በዘላቂነት ይሠራል ያሉት ከንቲባ አዳነች÷ ለዚህም የተባባሪ አካለትን ያልተቋረጠ ድጋፍ እንደሚሻ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡
የአገራችን ሁለንተናዊ ክብር የሚለካው የእያንዳንዱ ዜጋ ተጠቃሚነትና ክብር ሲረጋገጥ ነው ያሉት ከንቲባዋ÷ ለዜጎች የኑሮ መሻሻል ሁላችንም በየደረጃው ማህበራዊ ኃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል ነው ያሉት።
ከጸጥታ አካላትና ተቋማት ጋር በመቀናጀት የከተማችንን ሰላም መጠበቅና ልማታችንን ማስቀጠል ይገባናል ማለታቸውን የከንቲባ ጽሕፈት ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!