አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው የህወሓት ቡድን ዳግም የከፈተውን ጦርነት የሚያወግዝ ሠላማዊ ሰልፍ በአሜሪካ ዋሺንግተን ዲሲ እየተካሄደ ነው።
ሰልፉ “በሀገር ሕልውናና አንድነት አንደራደርም!” በሚል መሪ ሀሳብ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ፊት ለፊት እየተካሄደ ይገኛል።
ሠላማዊ ሠልፉ አሸባሪው ህወሓት ዳግም የከፈተውን ጦርነት ለማውገዝና የሀገርን ሕልውና ለማስጠበቅ እየተሳተፉ ላሉ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ለጸጥታ ኃይሎችና ዜጎች ድጋፍና አጋርነትን የመግለጽ ዓላማ እንዳለው የሰላምና አንድነት ለኢትዮጵያ ዲሲ ግብረ ኃይል ገልጿል።
የአሜሪካ መንግስት፥ ኢትዮጵያና ኤርትራ ላይ ያለው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በመከባበርና በሁለትዮሽ የጋራ ጥቅም ላይ ያተኮረ እንዲሆን የሚያሳስቡ መልዕክቶችም በሰልፈኞቹ ተላልፈዋል።
በሰላማዊ ሰልፉ ከኢትዮጵያውያን በተጨማሪ ትውልደ-ኢትዮጵያውያንና ሌሎች የኢትዮጵያ ወዳጆች ተሳትፈዋል።
የሰላምና አንድነት ለኢትዮጵያ ግብረ ኃይል ሰልፉን ከሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ጋር በትብብር እንዳዘጋጀውም መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል።