ስፓርት

ቼልሲ አሰልጣኝ ቶማስ ቱሼልን አሰናበተ

By ዮሐንስ ደርበው

September 07, 2022

አዲስ አበባ ፣ ጳጉሜን 2 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የእንግሊዙ እግር ኳስ ክለብ ቼልሲ አሰልጣኝ ቶማስ ቱሼልን ማሰናበቱን አስታወቀ።

ክለቡ ከትናንት ምሽቱ የዳይናሞ ዛግሬቭ የቻምፒየንስ ሊግ ሽንፈት በኋላ አሰልጣኙን ማሰናበቱን አስታውቋል።

አዲሱ የክለቡ ባለቤት ቴድ ቦህሊ የአሰልጣኞች ቡድን አባላትን ክለቡን እንዲመሩ በጊዜያዊነት ተክተዋቸዋል።

የ49 አመቱ ጀርመናዊ አሰልጣኝ በምዕራብ ለንደኑ ክለብ ለ20 ወራት በአሰልጣኝነት ቆይተዋል።

ቼልሲ በዘንድሮው የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር መልካም የሚባል ጅማሮ ካለማድረጉም በላይ ካለፉት 16 የሊግ ጨዋታዎች ሰባቱን ብቻ አሸንፏል።

ከዚህ ባለፈም አሰልጣኙ ከተጫዋቾቹ እና ከክለቡ የቦርድ አባላት ጋር ያላቸው ግንኙነት መሻከሩን መረጃዎች ያመላክታሉ።

የክለቡ ባለቤትም አዲስ አሰልጣኝ ለመቅጠር “ትክክለኛው ጊዜ አሁን ነው” የሚል እምነት እንዳላቸው ክለቡ በይፋዊ ገጹ አስነብቧል።

ቱሼል ከቼልሲ ጋር የቻምፒየንስ ሊግ፣ የአውሮፓ ሱፐር ካፕ እና የዓለም ክለቦች ዋንጫን ማሸነፍ ችለዋል።