አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከኡራዔል ወደ ወሎ ሰፈር የሚወስደውን አዲስ መንገድ የሠላም ጎዳና ብሎ ሰየመ፡፡
በሠላም ጎዳና ሥያሜ መርሐ-ግብር ላይ የአስተዳደሩ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ እና የኢፌዴሪ የሠላም ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ ብናልፍ አንዷለም ጨምሮ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
ዛሬ የተሠየመው የሠላም ጎዳና፥ የሠላም ቀንን ምክንያት በማድረግ ነው።
በመረሐ- ግብሩ ላይ ከንቲባ አዳነች፥ ጎዳናው የተሰየመው ለቅርብ እና ለሩቅም ወዳጆች የኢትዮጵያ ጉዞ የሠላም መሆኑን እንዲያውቁ ነው ብለዋል።
ከንቲባዋ ዛሬም ቢሆን ኢትዮጵያ አስቀድማ ለሠላም ዘርግታው የነበረው እጇ አለመታጠፉን ጠቁመዋል።
የኢፌዴሪ የሠላም ሚኒስትር አቶ ብናልፍ አንዷለሞ በበኩላቸው፥ የከተማ አስተዳደሩ ለሠላም ለሰጠው የላቀ ስፍራና ለጎዳና ስያሜው አመስግነዋል።
ለሰላም አስፈላጊውን ሁሉ መስዋዕትነት ከፍለን ሁላችንም በአንድነት የሀገራችንን ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ልንሰራ ይገባልም ነው ያሉት።
በመርሐ-ግብሩ ላይ የተገኙ የተለያዩ የሐይማኖት አባቶችም፥ የሐይማኖት አባቶች የኢትዮጵያ ወጣቶች ሰርተው የሚለወጡባትና አረጋውያን የሚጦሩበት ሀገር እንድትሆን እንዲፀልዩ ማሳሰባቸውን ከከንቲባ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።