ዓለምአቀፋዊ ዜና

ፑቲን እና ሺ ጂንፒንግ ከሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ሊገናኙ ነው

By Alemayehu Geremew

September 08, 2022

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሜር ፑቲን እና የቻይናው አቻቸው ሺ ጂንፒንግ በቀጣይ ሣምንት ኡዝቤኪስታን በሚካሄደው የሻንጋይ የትብብር ድርጅት ጉባዔ ላይ ይገናኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

መሪዎቹ በፈረንጆቹ መስከረም 15 እና 16 በሚካሄደው ጉባዔ ተገናኝተው የጎንዮሽ ውይይት እንደሚኖራቸው ለመገናኛ ብዙኃን የገለጹት በቻይና የሩሲያ አምባሳደር አንድሬ ዴኒሶቭ መሆናቸው ነው የተገለጸው፡፡

ሩሲያ እና ቻይና የምዕራቡን ዓለም ወቀሳ እና ማዕቀብ በመቃወም አሁን ላይ የኢኮኖሚ ትብብራቸውን ማሳደጋቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ።

በተለይ በቅርብ ጊዜያት ሩሲያ ከአሜሪካ እና አጋሮቿ ጋር ያላት ግንኙነት እየሻከረ መምጣቱን አልጀዚራ በዘገባው አመላክቷል።

አሁን ላይም ከቻይና ጋር ያላት ግንኙነት ይበልጥ “ገደብ የለሽ” ወደ ሆነ ወዳጅነት ማደጉንም ነው ዘገባው ያመላከተው።

የሩሲያው ጋዝፕሮም በወጪ ንግድ ለቻይና ጋዝ ለማቅረብ እና ክፍያውንም በቻይና መገበያያ ገንዘብ ዩዋን እና በሩሲያ መገበያያ ገንዘብ ሩብል ለመፈጸም ማክሰኞ ዕለት ሥምምነት ላይ መድረሱንም ዘግቧል፡፡

ከዩክሬን – ሩሲያ ግጭት ወዲህ ሩሲያ ይህን ውሳኔ ያሳለፈችው በአሜሪካ የገንዘብ ሥርዓት ላይ ያላትን ጥገኝነት ለመቀነስ እና ዶላርን ላለመጠቀም መሆኑም እየተነገረ ነው፡፡