የሀገር ውስጥ ዜና

የጉራጌ  እና የጎፋ ዞኖች ለሀገር መከላከያ ሰራዊት የሰንጋ ድጋፍ አደረጉ

By Mikias Ayele

September 08, 2022

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የጉራጌ  እና የጎፋ ዞኖች ለሀገር መከላከያ ሰራዊት 626 የእርድ ሰንጋ ድጋፍ አድርገዋል፡፡

የጉራጌ ዞን የብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ክፍሌ ለማ ÷ አሸባሪው ህወሓትን  ለመደምሰስ በሚደረገው ጥረት የዞኑ ህዝብ ከመከላከያ ሰራዊት ጎን መቆሙን  ገልፀዋል፡፡

አሸባሪው የህወሓት ቡድን የሰላም ጥሪን  እንደ ሽንፈት በመቁጠር  ያደረገው 3ኛ ዙር ወረራ እስኪቀለበስ ድረስ የዞኑ ህዝብ ከመከላከያ ጎን በመቆም ደጀንነቱን እያሳየ ይገኛል ብለዋል።

በቀረበው ሀገራዊ የድጋፍ ጥሪ መሰረትም 373 ሰንጋዎች፣ 159 የበግና የፍየል ሙክቶች፣ 96 ኩንታል ስኳር፣ 120 ኩንታል በሶ ማሰባሰብ መቻሉን  ሃላፊው ገልፀዋል፡፡

ድጋፉ በገንዘብ ሲተመን 30ሚሊየን 624 ሺህ 675 ብር እንደሚሆን መግለፃቸውን ከዞኑ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በተመሳሳይ የጎፋ ዞን የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ የህይወት መስዋዕትነት እየከፈለ ላለው ጥምር ጦር 253 ሰንጋዎች፣ 239 በግና ፍየል እንዲሁም 293 ኩንታል በሶ እና 18 ኩንታል ስኳር ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል።

የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶክተር ጌትነት በጋሻው እንደገለጹት÷ሀገርን የሚያስቀድም ህዝብ ባለቤት በመሆናችን  በአጭር ቀናት ይህን ያክል ሀብት ማሰባሰብ ተችሏል ማለታቸውን ከደቡብ ክልል ከሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡