የሀገር ውስጥ ዜና

የጤና ሚኒስቴር ያሰባሰበውን የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ለአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ አስረከበ

By Mikias Ayele

September 08, 2022

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የጤና ሚኒስቴር ከተጠሪ ተቋማትና ሠራተኞቹ ያሰባሰበውን የትምህርት ቁሳቁስ ለአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ አስረከበ።

ድጋፉን ያስረከቡት የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ÷ ይህኛው ድጋፍ የበፊቶቹ ጊዜያትድጋፎች አንዱ አካል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ዓላማውም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ወላጆችን ካለባቸው ጫና ማሳረፍ ነው ብለዋል ።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከተሰጠው ዋነኛ ተልዕኮ በተጨማሪ የተለያዩ የበጎ አድራጎት ሥራዎች ላይ እየተሳተፈ እንደሚገኝም ሚኒስትሯ ገልጸዋል፡፡

ከ 1 ሚሊየን በላይ ዜጎች በጤና ሚኒስቴር የነፃ የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ  መደረጉንም ነው የጠቆሙት፡፡

ባለፉት ዓመታት በሥፋት ሲተገበር በቆየው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ÷  የጤና ሚኒስቴርም በአዲስ አበባ እና በጋምቤላ ክልል የአቅመ ደካማ አረጋውያንን ቤት በማደስ እንደተሳተፈም ገልጸዋል።

ድጋፉ ለ900 ተማሪዎች የሚከፋፈል ሲሆን በወቅቱ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አድማሱ ደቻሳ  ተቀብለዋል፡፡