አዲስ አበባ ፣ ጳጉሜን 3 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አዲስ ዓመት ኢትዮጵያውያን በየዓመቱ በታላቅ ስሜት ከሚያከብሯቸው በዓላት አንዱ ነው።
በኢትዮጵያ የዘመን ስሌት መሰረት፥ ዓመት ተሸኝቶ አዲስ ዓመት የሚጀመርበት ዕለት “ዓውደ ዓመት፣ አዲስ ዓመት፣ ዕንቁጣጣሽ፣ የዘመን መለወጫ” እየተባለ ይጠራል፡፡
ሊቃውንት የሰው ልጅ እንደ ዕፅዋት ሁሉ በመስከረም ወር በተስፋ ስሜት ይለመልማል ይላሉ።
ከዋዜማው ጀምሮ በየቤቱ በከተማ እና በገጠር ሁሉም እንደ ዕድሜው እና ጾታው “እዮሐ አበባዬ መስከረም ጠባዬ፤ እንኳን ከዘመን ዘመን አሸጋገራችሁ” በማለት መልካም ምኞት ይለዋወጣል፡፡
የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ወራት ከመስከረም 1 ቀን ይጀምራል፤ ለዚህ ደግሞ የራሱ የሆነ አመጣጥና ታሪክ እንዳለው ሊቃውንት ይናገራሉ፡፡
ይህም ከሀገሪቱ ተፈጥሯዊ ክስተቶች በመነሳት መስከረም 1 የወራት መጀመሪያ እንዲሆን ተደረገ ይላሉ።
ኢትዮጵያ ከሌሎች የዓለም ሀገራት በተለየ በራሷ ስያሜ የምትሔድና ለእያንዳንዱ ስያሜም ማስረጃና ምክንያት እንዳላት ያነሳሉ፡፡
ዘመን ተለወጠ ሲባል ለውጡ በወራቱ መፈራረቅ ብቻ እንዳልታጠረ ይታመናል፤ ስለሆነም ከሰው ልጆች እንቅስቃሴ እና የኑሮ ብሎም የሥራ ሁኔታ ጋር የተያያዙ ሁኔታዎች ሁሉ እንደሚለወጡ ይታሰባል፡፡
ይህም ከሰው ልጅ ዕድሜ ጀምሮ በተማሪው፣ በአርሶ አደሩ፣ በነጋዴው፣ በሠራተኛውና በተፈጥሮም ላይ ከዘመን ጋር የሚታይ ለውጥ ይኖራል።
ዓለም አዲስ ዓመትን ዕኩለ ለሊት ላይ በደማቅ የ “እርችት” ትርዒት የዋዜማ ድግሶች ይቀበላል።
በበርካታ ሀገራት ያለው የሰዓት አቆጣጠር አዲስ ቀንን እኩለ ለሊት ላይ አንድ ብሎ ይጀምራል። ከዚያም ጋር ተያይዞ አዲስ ዓመትን ተቀበልን ብለው የሚያምኑትም በዚሁ እኩለ ለሊት ላይ ነው።
ይህ የአከባበር ዘይቤም በሀገራችን የተለመደ ይመስላል።
አዲስ ዓመትን መሰረት አድርገው በሚሰናዱ የምሽት ድግሶችም ሆነ በሌሎች ሁነቶች ላይ የአዲስ ዓመት ቆጠራ የሚከናወነው እና አዲስ ዓመት ገባ ተብሎ የሚታወጀው እኩለ ለሊት ላይ መሆኑን እንታዘባለን።
እናም የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት ስንት ሰዓት ላይ ይገባል የሚለው ማከራከሩ አልቀረም።
ከዘመን ለውጥ ጋር ተያይዞ ሐይማኖታዊ አስተምህሮው ምን ይላል?
በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የየረር መካነ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን የትርጓሜ መጻሕፍት መምህሩ መላዕከ ታቦር ኃይለ ኢየሱስ ፈንታሁን÷ ስለ ዘመንም ሆነ ቀን መግቢያ እና መውጫ ለማወቅ አንድ መሠረታዊ እና ሁላዊ ሕግ አለ ይላሉ፡፡
ይኸውም “አንድ ቀን ማለት 24 ሠዓት ነው” የሚለው ሐቅ መሆኑን ይገልጻሉ፤ የተፈጥሮ ሕግ መሆኑን በማንሳት።
ይህን ሐቅ በመመርኮዝ አንድ ቀን “አቆጣጠሩ ከሌሊት ጀምሮ ቀን ላይ ይጨርሳል” እንደ መላዕከ ታቦር ገለጻ፡፡
ይህንም በምሳሌ ሲያስረዱ÷ በኢትዮጵያ የዘንድሮው የዘመን መለወጫ የሚገባው (የሚጀምረው) ከቅዳሜ ምሽት 1 ሠዓት ጀምሮ መሆኑንም ነው የሚናገሩት።
በእብራውያን (እስራኤላውያን) የጊዜ ስሌት ደግሞ ማንኛውም ቀን የሚገባው ከምሽቱ 12 ሠዓት ጀምሮ መሆኑን ያስረዳሉ። ይህ አስተምህሮ በዘመን መለወጫ ብቻ እንደማይገደብና በሁሉም የቀናት ስሌት ላይ እንደሚሠራም ነው የሚናገሩት።
ይሁን እንጅ ይህ የጊዜ ስሌት ለጾም መግቢያ እና መውጫ አይሠራም ነው የሚሉት መምህር መላዕከ ታቦር ኃይለ ኢየሱስ፥ ምክንያቱ ደግሞ የጾም ቀን ወይም ዕለት መግቢያም ሆነ መውጫ እንደየሀገራቱ የኑሮ ዘይቤ ስለሚወሰን መሆኑን ያስረዳሉ።
የጾም እና የማንኛውም ቀን አገባብ እኩል ይሁን ቢባል በሕዝቦች የአኗኗር ሁኔታ ላይ ችግር ያስከትላል፤ ሊቃውንትና አባቶችም ይህን ስለሚያውቁ ነው የጊዜ አሰላሉን በጥንቃቄ ያዘጋጁት ብለዋል፡፡
መላዕከ ታቦር ከላይ እንዳነሱት÷ የዘመን መለወጫ ቅዳሜ ምሽት 1 ሠዓት ላይ የሚገባ ቢሆንም አዋጁ የሚታወጀው ግን ከ12 ሠዓታት በኋላ ወይም ከጠዋቱ 1 ሠዓት አካባቢ ነው፡፡
ይህ የሆነውም አዋጅ በጨለማ ስለማይነገር እና ብስራት ወይም አዋጅ የሚታወጀው በብርሃን ስለሆነ የግድ እስከሚነጋ መጠበቅ አስገዳጅ በመሆኑ እንደሆነም ያብራራሉ።
በዚሁ መሠረት የዘንድሮው ዘመን መለወጫ ቅዳሜ ከምሽቱ 1 ሠዓት ላይ ይገባል፤ መስከረም መጥባቱ የሚበሰረው ግን በዕለተ እሁድ ከጠዋቱ 1 ሠዓት አካባቢ ይሆናል፡፡
የተለያዩ ሀገራት የየራሳቸው የዘመን ስሌት እንዳላቸው ጠቁመው÷ የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር ስነ ፍጥረትን የተመረኮዘ መሆኑን አስረድተዋል መምህሩ፡፡
በዮሐንስ ደርበው