አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ቤጂንግ ለሚገኙ የአፍሪካ ኅብረት የሠላምና ጸጥታ ምክር ቤት አባላት በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ገለጻ ሠጡ፡፡
በመርሐ-ግብሩ ላይ በተ.መ.ድ የጸጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል በመሆን እያገለገሉ የሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት ከፍተኛ ዲፕሎማቶችም ተገኝተዋል ነው የተባለው፡፡
አምባሳደር ተሾመ ፥ የህወሓት ቡድን የኢትዮጵያ መንግስት ያቀረባቸውን የሰላም አማራጮች ሁሉ ወደጎን በመተው ድጋሚ ጥቃት በመክፈት በትግራይና በአጎራባች የአማራና የአፋር ክልሎች ዘግናኝ ግፍ እየፈፀመ ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ገና ከጥንስሱ ችግሮቹን በውይይት ለመፍታት ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱንም ነው ያስታወሱት፡፡
የአፍሪካ ኅብረትን ሰላም ለማስፈን እየተንቀሳቀሰ ቢሆንም የአሸባሪው ህወሓት ቡድን ግን የኅብረቱን ክብር ዝቅ በማድረግ የሠላም ሂደቱን አልቀበልም ማለቱን አምባሳደር ተሾመ ተናግረዋል፡፡
አምባሳደሩ አክለውም ፥ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ኅብረት የሠላም ሂደት እንደምትተማመን በመጠቆም ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ የሚለውን መርኅም አጥብቃ የምትከተል ሀገር መሆኗን ነው አጽንኦት ሰጥተው የገለጹት።
አምባሳደር በማጠቃለያቸው ፥ እኛ አፍሪካውያን በአንድነትና በትብብር ለጋራ ሠላምና ዕድገት ተግተን ልንሠራ ይገባል ብለዋል፡፡